በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ የሚመክረው 28ኛው የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ሁሉን አቀፍ ዕድገት ላይ እንደሚያተኩር ተገለጸ

ዛሬ በደቡብ አፍሪካ የሚጀምረው 28ኛው የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ሁሉን አቀፍ ዕድገት ላይ እንደሚያተኩር ተገለጸ፡፡

ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራት መፃኢ ብልጽግና መሠረት ያደረገው የመሪዎቻቸው ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ ዕድገት የማምጣት ችሎታ ላይ ነው።

በዚህ በፈጣን ለውጥ ውስጥ በሚገኘው 4ኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን ደግሞ ይህ ብቃት ከመሪዎቹ ይጠበቃል።

እ.አ.አ. ከመስከረም 4-6/2019 ዓ.ም ኬፕ ታውን፣ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሚካሄደው በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ የሚመክረው 28ኛው የዓለም የኢኮኖሚ ፎረምም ይህንኑ ትኩረት ያደረገ እንደሆነ ተገልጿል።

ፎረሙ ላይ ርእሳነ መንግሥታት እና ርእሳነ ሀገራትን ጨምሮ 1 ሺህ 100 የሚሆኑ የመንግሥታት ኃላፊዎች፣ የቢዝነስ እና የሲቪል ማኅበረሰብ ይገኛሉ።

የፎረሙ ዋና አጀንዳ ለሰፊው እና እያደገ ለመጣው የአፍሪካ የሠራተኛው ኃይል ዘላቂ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር አዲስ አጋርነት መመሥረት የሚል እንደሆነ ተጠቁሟል።

የመንግሥት ፖሊሲዎች እና ኃላፊነት የተላበሱ የቢዝነስ እንቅስቃሴዎች የበለጠ አካታች የሆነ ማኅበረሰብን ለመገንባት ያላቸው ሚናም ዋና የመወያያ አጀንዳ ይሆናሉ ተብሏል።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴም በፎረሙ ላይ ለመሳተፍ ኬፕ ታውን ደቡብ አፍሪካ ገብተዋል። (ምንጭ፦ ዎርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም ኦን አፍሪካ)