በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና  ከ27 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ለርሃብ አደጋ ተጋልጧል

የአየር ንብረት ለውጥ፣ ግጭት እና ምጣኔ ሀብታዊ አለመረጋጋት በአፍሪካ ቀንድ ከ27 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ለርሃብ አደጋ እንዲጋለጥ ምክንያት መሆኑ ይፋ ተደርጓል፡፡

የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ባለፈው ሳምንት በኬንያ ናይሮቢ በአደጋ መከላከል ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይቱ መጨረሻ ባወጣው መግለጫም አለም አቀፉ ማህበረሰብ አፋጣኝ ምላሽ ካልሰጠ በቀጣናው ተጨማሪ 20 ሚሊየን ሕዝብ ለርሃብ አደጋ ይጋለጣል ሲል ስጋቱን አስቀምጧል፡፡

ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ኢትዮጵያም በከፍተኛ ደረጃ የምግብ እጥረቱ ተጠቂ ሀገራት ሊሆኑ ይችላሉ ነው የተባለው፡፡

በቀጣናው እ.አ.አ በ2018 የተስተዋለው የዝናብ እጥረት፣ ግጭትና ምጣኔ ሀብታዊ አለመረጋጋት በ2019  እንደቀጠለ ነው ያለው ኢጋድ፤ ይህም የሀገራቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ፈታኝ እንደሚያደርገው አስጠንቅቋል፡፡

አሁን ያለው ሁኔታ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን ችግሩ የከፋ ነው፡፡

ዘ ኢስት አፍሪካን ጠቅሶ ሲጂቲኤን እንደዘገበው ችግሩን ለመቋቋም ዓለም አቀፉ ግብረ ሰናይ ድርጅት ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ ኢጋድ ጠይቋል፡፡