ኬንያ ገንዘብ ከመቀየሯ ጋር ተያይዞ ከሰባት ቢሊዮን ሺልንግ በላይ ጥቅም አልባ ሆነ

የኬንያ ማዕከላዊ ባንክ እንዳሳወቀው ኬንያ የመገበያያ ገንዘብ ከመቀየሯ ጋር ተያይዞ ከ95% በላይ የሚሆነው የአንድ ሺ ሺልንግ ተመልሶ በአዲሱ ተተክቷል።

በዚህ መካከል ግን መሃል ላይ ተንሳፎ የቀረ ገንዘብ እንዳለም ተገልጿል።

"ይህ ማለት 7.3 ቢሊዮን ሺልንግ ጥቅም አልባ ሆኗል፤ እንደ ወረቀት ነው የሚቆጠረው" በማለት የባንኩ አስተዳዳሪ ፓትሪክ እንጆሮጌ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።

ባንኩ እንዳሳወቀው አዲስ የመገበያያ ገንዘብ የታወጀው ሰኔ አንድ ቀን ሲሆን፣ ከዚያ ዕለትም ጀምሮ ሲዘዋወር የነበረ 217 ሚሊዮን ሽልንግም ተገኝቷል።

ከመስከረም ሃያ ጀምሮ አሮጌው የመገበያያ ገንዘብ ከጥቅም ውጭ ሆኗል።

በዚህ ወቅትም ከሶስት ሺ የሚበልጡ አጠራጣሪ ልውውጦች ሪፖርት የተደረጉ ሲሆን፣ በሚመለከተው የመንግሥት አካልም ምርመራ እንደሚደረግም ኢንጆሮጌ አክለው ገልፀዋል።

የገንዘብ ቅየራው በሃገሪቷ ውስጥ የተንሰራፋውን ሙስና ለማስቀረትና ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርንም ለመቆጣጠር እንዲያስችል ነው።

አፍሪካ ታክስ ጀስቲስ ኔትወርክ የተባለ ድርጅት እንዳሳወቀው በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ምክንያት ኬንያ በየአመቱ 400 ሚሊዮን ዶላር እንደምታጣ አስታውቋል።

ባንኩ እንዳስታወቀውም የገንዘብ ቅይይሩ መሳካቱንና ከዚህ በኋላ ስርአት ባለው መንገድ የገንዘብ ዝውውር እንደሚከናወን ነው። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)