ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ በሶማሊያ በሚገኘው የአልሻባብ አሸባሪ ቡድን ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሟን የፔንታጎን ፕሬስ ሴክሬተሪ አድሚራል ጆን ኪርቤይ አስታወቁ ።
የዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ የጮር ጄቶች ድብደባ የፈጸሙት በሶማሊያ ሳኮው በተባለ ሥፍራ ላይ ሲሆን የእስልምና አክራሪ ታጣቂ ቡድኑ ከፍተኛ አመራርን ሊላማ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል ።
እስካሁን ድረስ በአየር ድብደባው ምክንያት ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ ያልታወቀ መሆኑንና አስፈላጊ ከሆነ በአየር ጥቃቱ የደረሰው ጉዳት እንደታወቀ ተጨማሪ መረጃ ሊሠጥ እንደሚችል አድሚራ ኬርባይ ተናግረዋል ።
በሶማሊያ አልሻባብ ቡድን ላይ የተፈጸመው የአየር ጥቃት በሰው አልባ አውሮፕላኖች የተካሄደ መሆኑን የፔንታጎን ኃላፊው አመልክተዋል ።
ባለፈው ቅዳሜ ሁለት የሶማሊያ የጦር አዛዦች የአልሻባብ ከፍተኛ አመራሮችንም መያዛቸውን መናገራቸው የሚታወስ ሲሆን የአልሻባብ የደህንነት ዋና አዛዥ ዘካሪያ እስማኤል አህመድ ሀርሲ በኢል ዋክ ከተማ አቅራቢያ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገልጿል ።
የአልሻባብ ታጣቂ ቡድን ባለፈው ሳምንት ሞቃዲሾ በሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስካባሪ ኃይል ወታደራዊ ይዞታ ላይ ጥቃት በመፈጸም የኡጋንዳ ወታደ ችና ሲቪሎች እንዲገደሉ ካደረገ በኋላ የቡድኑ ወሳኝ አመራሮች እየታደኑ ይገኛሉ ።
አልሻባብ በበኩሉ በሞቃዲሾ የአፍሪካ ህብረት ይዞታ ላይ የፈጸመው ጥቃት ዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ የቡድኑ መሪ በሆነው ጎዳኔ ላይ ለፈጸመችው ግድያ የበቀል ምላሽ እንደሚሆን ገልጿል ።
የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የቀድሞ የአልሻባብ መሪ ጎዳኔ ያለበት ቦታ ለጠቆመ ግለሰብ የ7 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ሽልማት መሥጠቱ ይታወሳል ። ( ምንጭ : ሲኤን ኤን )
(ትርጉም : በሰለሞን ተስፋዬ)