በስደት በዓለ ሲመታቸውን የፈጸሙት አዲሱ የጋምቢያ ፕሬዝዳንት አዳማዋ ባሮ ወደ አገራቸው ተመለሱ።
በጋምቢያ ባለፈው ታህሳስ በተካሄደ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ የነበሩት አዳማዋ ባሮ የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት አገሪቱን ጥለው መውጣታቸውን ተከትሎ ስልጣናቸውን ለመረክብ ነው ወደ ዋና ከተማዋ ባንጁል ዛሬ የተመለሱት።
ፕሬዝዳንት ባሮው በባንጁል አየር ማርፊያ ሲደርሱ ደጋፊዎቻቸው ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
አዳማዋ ባሮ ባለፈው ታህሳስ በምርጫው ካሸነፉ በኃላ ፕሬዝዳንት ጃሜ ስልጣናቸውን እንደማይልቁ ማስታወቃቸውን ተከትሎ በጎረቤት ሴኔጋል ሆነው ነብር በዓለ ሲመታቸውን ጭምር በመፈፀም የአገራቸውን ሁኔታ በቅርብት ሲከታተሉ የነበሩት።
አሁን ላይ ደስተኛ ነኝ፤መጥፎው ጊዜ አልፏል ያሉ ፕሬዝዳንት ባሮው፣ በፍጥነት ካቢኒያቸውን በማዋቀር አገራቸውን ወደነበረችበት መረጋጋት ለመመለስ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
ጋምቢያን ለ22 ዓመታት የመሩት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ያህያ ጃሜ በምዕራብ አፍሪካ አደራዳሪዎች አማካኝነት አገር ጥለው በስደት ለመኖር ከወጡ በኃላ፣ የቀጠናው ጦር ለአዲሱ ፕሬዝዳንት ጥበቃ እያደረገ መሆኑን ተመልክቷል-(ኢብኮ) ።