የኢትዮጰያና ደቡብ ሱዳን ግንኙነት መቼም ሊቋረጥ የማይችል ነው–የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ መሆኑን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴንግ አሎር አስገነዘቡ ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዴንግ አሎር  እንደገለጹት "የሁለቱ አገራት ግንኙነት በጠንካራ የጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ነው፤ በየጊዜው የሚተባበሩባቸው የሁለትዮሽና አህጉራዊ አጀንዳዎችም እያደጉ ነው።"

"የአገራቱ  የሁለትዮሽ ግንኙነትን አስመልክቶ ባሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ያሰራጩት ዘገባ መሰረተ ቢስ ወሬ ነው" ብለውታል።

"ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን እውነተኛ ወዳጅ ነች" ያሉት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የአገራቱ ወዳጅነት መቼም ሊቋረጥ የማይችል እንደሆነ ነው የገለጹት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ባለፈው ጥቅምት በጁባ የሥራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን ከፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ ተነጋግረው ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።

አገራቱ በተለይም በንግድና ኢንቨስትመንት ትስስርና ጥበቃ፣ በሠላምና ፀጥታ፣ በመሰረተ ልማት ትስስር፣ በጦር መሳሪያ የታጠቁ አማፂያንን አለመርዳትና ሌሎች የጋራ ጥቅሞችን በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ዙሪያ በቅንጅት ለመስራት ተስማምተዋል።

እንደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገለፃ አገራቱ ከዚህ በፊት የደረሱባቸውን ስምምነቶች ስለመተግበርና ተጨማሪ ግንኙነቶችን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ለመስራት የሚጥሩ አገራት እንጂ ወዳጅነቱን ሊያቋርጡ እንደማይችሉ ነው።

ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር እንደ አገርም ሆነ እንደ ኢጋድ መሪነቷ ለአገራቸው እየሰጠችው ባለው ድጋፍ ደስተኛ መሆናቸውንም ገልጸዋል-(ኢዜአ)።