የጊኒ ሪፐብሊክ ፕሬዚደንት የሆኑት አልፋ ኮንዴ እኤአ በ 2017 የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ ።
ዛሬ በተካሄደው 28ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ የተለያዩ ክቡራን እንግዶች በተገኙበት በተከናወነው ምርጫ የምዕራብ አፍሪካ ተወካይ የሆኑት አልፋ ኮንዴ ድምጽ በማግኘታቸው ከአምናው የአፍሪካ ህብረት መሪዎች ሊቀመንበር ከሆኑት የቻድ ፕሬዚደንት ኢድሪስ ዴቢ ሥልጣናቸውን ተረክበዋል ።
ተመራጩ ሊቀመንበር ፕሬዚደንት አልፋ ኮንዴ “ አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት የተለያዩ ድርጅቶች ያላትን አነስተኛ የተወካይነት መቀመጫ ለማሳደግ እንደሚሠሩና የአፍሪካን ድምጽ እንዲሰማ ጥረት እንደሚያደርጉ ” አስታውቀዋል ።
እንደ አልፋ ኮንዴ ገለጻ አፍሪካ በአንድ ድምጽ የምትናገርና በምንም መልኩ ቢሆን የማትከፋፈል መሆኗንና በአፍሪካ አገራት መካከል ይበልጥ ትብብርን ለማጉልበት ይሠራሉ ።
አፍሪካ የተጋረጠባትን የወጣቶች ሥራ አጥነት ፣ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና የኃይል ልማትን ለማጠናከር በሥልጣን ዘመናቸው ተገቢ የልማት ሥራዎችን ማከናወን እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸዋል ።
የተለያዩ የሃይል ምንጮች በማስፋፋት ሥራዎች ላይ በማተኮር የሃይል አቅርቦት እጥረት ያለባቸውን 700 ሚሊዮን አፍሪካውያንን ለመደገፍ እንደሚተጉ አረጋግጠዋል፡፡
ፕሬዚደንት አልፋ ኮንዴ ወጣቶችን ብዛት ማዕከል ያደረጉ የልማት ሥራዎችን በአህጉሪቱ እንዲካሄዱ ለማድረግ ግፊት ለማሳደር ማቀዳቸውን አስረድተዋል ።
የተሰናባቹ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ፕሬዚደንት ኢድሪስ በበኩላቸው በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት ተገቢውን ሚና እንደተጫወቱና የተቋማትን በለውጥ ሂደት እንዲያልፉ የማድረግ ሥራዎችን ማከናወናቸውን አስገንዝበዋል ።
28ኛው የአፍሪካ የመሪዎች ስብሰባ በነገው ዕለት ቀጣዩን የአፍሪካ መሪዎች ሊቀመንበር እንደሚመርጥ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።
(ትርጉም- በሰለሞን ተስፋዬ)