ተመድ የአፍሪካ የልማት ግቦች እንዲሳኩ ድጋፍ እንደሚያደርግ ዋና ጸሐፊው አረጋገጡ

የተባሩት መንግስታት ድርጅት በአፍሪካ  ዘላቂ የሥልጣን ሽግግር እንዲረጋገጥና  የልማት ግቦች እንዲሳኩ ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ አረጋገጡ ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ዛሬ በ28ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ድርጅቱ በአፍሪካ ዘላቂ የሥልጣን ሽግግር እንዲረጋገጥና የልማት ግቦች እንዲሳኩ ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል ።

የክብር እንግዳው ጉተሬዝ አፍሪካ በፈጣን ምጣኔ ሃብታዊ እድገት እየገሰገሰች መሆኗን ነው ያረጋገጡት ፡፡

አፍሪካ  በማህበራዊና ኢኮኖሚ ዘርፎች መሻሻሎችን በማሳየት ሽብርተኝነት  በመዋጋትም ረገድ  የተሻለ ውጤት እያስመገበች እንደምትገኝ ገልጸዋል ።  

አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምና ጸጥታ ማስከበር ተልዕኮ ትልቁን ድርሻ እየተወጣች መሆኑን አመልክተዋል።

በ2030 ለተነደፉ የዓለም ዘላቂ የልማት ግቦች ስኬት፣ በአፍሪካ ሰላምና ጸጥታ ለማስፈንና በሰብአዊ መብት ጉዳዮች በአህጉሪቱ ከሚገኙ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ማህበራት ጋር ያላቸውን ግነኙነት እንደሚያጠናክሩ አስታውቀዋል ፡፡

ድርጅታቸው ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመሆን  አህጉሪቱ  ስደተኞችን   በበጎ መልኩ  በመቀበል  የተለመደ  ትብብር  እየተደረገ መሆኑን  ገልጸዋል ።

የአፍሪካ ህብረት መዋቅር እንዲሻሻልና የህብረቱ ጸጥታ ምክር ቤት እንዲጠናክር ድርጅቱ በዘላቂነት የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል