የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት የቀድሞ የቻድ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሙሳ ፋቂ በሥልጣን ዘመናቸው በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን እንደሚሠሩ ተናግረዋል ።
ሙሳ ፋቂ ማህማት ልምድ ያላቸው የ56 ዓመት ፖለቲከኛ ሲሆኑ በተለያዩ ፈታኝ የሥራ ኃላፊነት ተመድበው ብቃታቸውን ማሳየታቸው ተገልጿል ።
ሙሳ ፋቂ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ጊዚያዊ መቀመጫ የቻድ ተወካይ እጩ መሆን የቻሉ ሲሆን ለአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነርነት መመረጥ ችለዋል ።
የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ፀጥታ ኮሚሽን እኤአ በ2013 በናይሮቢ ከተማ በተካሄደው ጉባኤ የመሪነት ሚና የተጫወቱት ሙሳ ፋቂ በአፍሪካ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ ተገቢውን ሚና ተጫውተዋል ።
ሙሳ ፋቂ በአገራቸው በጠቅላይ ሚንስትርነትና በውጭ ጉዳይ ሚንስትርነት ከማገልገላቸውም በላይ ቻድ ባካሄደችው የፀረ -ሽብር ዘመቻ ከሊቢያ ፣ ማሊ ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ማዕከላዊ የአፍሪካ ሪፐብሊክና ከሳህል አካባቢ አገራት ጋር የተቀናጀ የዘመቻ እንቅስቃሴ ለማድረግ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል ።
በፕሪቶሪያ ዩኒቨርስቲ የሰላምና ፀጥታ ጥናት ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ሌሲል ሎውን ቫድራን በበኩላቸው ለዶቼዴሌ እንደገለጹት ሙሳ በትውልድ አገራቸው ሽብርን ለመግታት ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ የሚታወቁ መሆናቸውን ተናግረዋል ።
የቀድሞ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ዶክተር ድላሚኒ ዙማ ግጭት በሚባዛባት አፍሪካ በተለያዩ አገራት ቀውሶች ሲከሰቱ ችላ በማለት እንደሚተቹ ቫደራን አስረድተዋል ።
በተለይ አምስቱ የሳህል አገራት የሆኑት ሞሪታኒያ ፣ ማሊ ፣ኒጀር፣ ቡርኪና ፋሶ እና ቻድ በፈጠሩት የፀረ-ሽብር ዘመቻ ጥምረት ሙሳ ፋቂ የአገራቱ የውጭ ጉዳይ የሚንስትሮቹ ሊቀመንበር በመሆኑን ከፍተኛ ኃላፊነታቸውን እንደተወጡ ቫድራን አብራርተዋል ።
የቻድ ወታደሮች በሙሳ ፋቂ መመረጥ የተሰማቸውን ደስታ በቻድ ዋና ከተማ ኒጃሚና አቅራቢያ በሚገኝ ወታደራዊ ሠፈር መግለጻቸውም ተመልክቷል ።
በተጨማሪም ሙሳ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነርነት መመረጥ አውሮፓንም ሆነ አሜሪካን የሚያስደስት ያስደስታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የተለያዩ እስላማዊ አክራሪ ቡድኖችና ቦኮሃራምን ለመዋጋት ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል ።
የፈረንሳይ የፀረ-ሽብር ኦፕሬሽን ዋና መቀመጫም በቻድ መሆኑ ይበልጥ ከአፍሪካ ህብረት ጋር ያለውን ግንኙነት ያጠናክረዋል ተብሎ ይጠበቃል ።
የአፍሪካ ህብረት ከስድስት ወራት በፊት ባካሄደው የህብረቱ የኮሚሽነር ምርጫ አንድም እጩ ከ ሁለት ሦስተኛ በላይ ድምጽ ያለገኘ በመሆኑ ምርጫው በጥር ወር እንዲካሄድ በተወሰነው መሠረት ከትናንትና በስተያ ሙሳ ፋቂ ከኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አሚና ሞሃመድ የተሻለ ድምጽ በማግኘት ኮሚሽነር መሆን ችለዋል ።
አዲሱ ተመራጭ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ የህግ ትምህርታቸውን በብራዛቪል እና ፓሪስ የተከታታሉ ሲሆን በሥልጣን ዘመናቸው በአፍሪካ ከጠመንጃ ተኩስ ይልቅ የአፍሪካውያን ባህላዊ ዝማሬዎችና የፋብሪካዎች ድምጽ እንዲሰሙ በትኩረት እንደሚሠሩ ተናግረዋል ።
በእሳቸው የአራት ዓመት ቆይታም በአፍሪካ ልማትና የፀጥታ ጉዳይ ቅድሚያ የሚሠጣቸው አጀንዳዎች እንደሚሆኑንና አስፈላጊም ከሆነ በአፍሪካ ህብረት ድርጅትም ለውጥ እንደሚያደርጉ አስገንዝበዋል ። ( ምንጭ ዶቼቬሌ )