ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አባልነት በጋራ መውጣትን ህብረቱ ወሰነ

 

የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራቱ ከአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አባልነት በጅምላ እንዲወጡ ጥሪ አስተላለፈ ::

የህብረቱ አባል ሀገራት አዲስ አበባ በተካሄደው የህብረቱ 28ኛ የመሪዎች ጉባኤ ላይ በጉዳዩ ዙሪያ ብርቱ ክርክር ማካሄዳቸውን ጠቅሶ ዛሬ ቢቢሲ ዘግቧል።

የውሳኔው የተወሰነ ክፍል ህብረቱ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ጋር በመነጋገር የዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቱ እንዲሻሻል እንደሚሰራ ነው የሚያመለክተው ።

የአለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እንዲቋቋም መነሻ የሆነውን የሮም ስምምነትን 34 የአፍሪካ ሀገራት መፈረማቸውን ነው የገለጸው ።

ይሁንና ናይጄሪያና ሴኒጋል ከአባልነት መወጣትን ተቃውመዋል።

ደቡብ አፍሪካና ብሩንዲ ፍርድ ቤቱ የሀገራትን ልዓላዊነትን የሚጻረርና በተለይም አፍሪካውያን ላይ ያነጣጠረ ኢ-ፍትሃዊ አካሄድ ነው በሚል አስቀድመው ለመውጣት መወሰናቸውን ነው ያስታወቀው ።

ፍርድ ቤቱ በበኩሉ በአፍሪካ በሚፈጸም የጦር ወንጀሎች ሰለባ የሆኑ ዜጎች ፍትህ እንዲያገኙ ማስቻል እንደሆነ በመግለጽ የሚቀርብበትን ክስ አልተቀበለውም ።