የሶማሊያ ባህር ላይ ጠላፊዎች አንድ የህንድ ንግድ መርከብ ጠለፉ

የሶማሊያ የባህር ላይ ጠላፊዎች በሶማሊያ ባህር ዳርቻ አንድ የህንድ የንግድ መርከብ መጥለፋቸው ተሰማ፡፡

ከበርካታ አመታት ወዲህ ይህ በሶማሊያ ባህር ዳርቻ አካባቢ የተካሄደ ሁለተኛው የባህር ላይ ጠለፋ መሆኑ ተነግሯል፡፡

በኤደን ባህረ ሰላጤ የንግድ መርከቦች እና ጀልባዎችን በማስተባበር እየሰራ የሚገኘው የብሪታኒያ የመርከብ ንግድ ድርጅት አገኘሁት ባለው መረጃ ፤ከአቡዳቢ ወደ ቦሳሶ ጉዞ በማድረግ ላይ ነበረች የህንድ ንግድ መርከብ ስኮትራ በተሰኘች ደሴት ስትደርስ በባህር ላይ ጠላፊዎች መጠለፏን አስታውቋል፡፡

የመርከብ ድርጅቱ ቃል አቀባይ ጠላፊዎቹ መርከቧን ወዴት እንደወሰዷ መረጋገጥ ባይችልም፤ መርከቧን አል ኩሳር የሚባል ቦታ ሳይወሰዷት እንዳልቀረ ገልጿል፡፡

የባህር ጠላፊዎቹ የንግድ መርከቧን ከ11 የመርከቧ ሰራተኞች ጭምር ያገቱ ሲሆን ፤ ጠላፊዎቹም በመርከቧ ተሳፍረዋል፡፡

እንደ ቢቢሲ ዘገባ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሶማሊያ መንግስት ፍቃድ የተሰጣቸው አሳ አስጋሪዎች ጨምሮ በርካታ የውጭ አሳ አስጋሪዎች በባህር ዳርቻዎቻቸው አሳ እያጠመዱ መሆናቸው ሶማሊያውያን እያስቆጣቸው ይገኛል፡፡

መቀመጫውን ብሪታኒያ ውስጥ የሆነው የባህር ላይ የደህንነት ድርጅት ሃላፊ ጊቦን ብሩክስ እንደተናገሩት ፤ ጠላፊዎቹ መርከቧንና የመርከቧን ሰራተኞች ለመልቀቅ ክፍያ ጠይቀዋል፡፡

የሶማሊያ ባህር ላይ ጠላፊዎች እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2012 ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ወር አንድ መርከብ ጠልፈው በፑንትላንድ የባህር ኃይል በከፈተባቸው ተኩስ መርከቧን መልቀቃቸው ይታወሳል-(ኤፍ ቢ ሲ) ፡፡