በሶማሊያ ሞቃድሾ በደረሰ ፍንዳታ ከ20 በላይ ሰዎች ሞቱ

 

በሶማሊያ መዲና ሞቅዲሹ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናትን ኢላማ ባደረገ የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ፍንዳታ በትንሹ 20 ሰዎች ተገደሉ፡፡

ፍንዳታው በመዲናይቱ በርካታ ቦታዎች የተሰማ ሲሆን ጥቃቱ በደረሰበት የሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ቅጽር ግቢ ውጪ ከፍተኛ ጭስ ሲትጎለጎል ታይቷል። ፍንዳታው የተከሰተው አንድ አጥፍቶ ጠፊ ቦምብ የተጠመደበትን መኪና ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በመውጣት ላይ ከነበሩ ተሽከርካሪዎች ጋር ካላተመ በኋላ እንደሆነ ስማቸው መግለጽ ያልፈለጉ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ ለጀርመን ዜና አገልግሎት (ዲፒኤ) ገልጸዋል፡፡

አንድ የሀገሪቱ ከፍተኛ የፖሊስን መኮንን እንደገለጹት ከማቾቹ ውስጥ አምስቱ ወታደሮች ሲሆኑ ስምንቱ ደግሞ በሚኒባስ ይጓዙ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡

በፍንዳታው በርካታ ወታደራዊ መኪናዎች ከጥቅም ውጭ መሆናቸውን ዲፒኤ ዘግቧል፡፡ መሰል ተደጋጋሚ ፍንዳታዎችን ሲያደርግ የቆየው እስላማዊ ታጣቂ ቡድን አልሻባብ ለዚህኛውም ጥቃት ኃላፊነቱን ወስዷል፡፡

ከ20 በላይ ወታደሮችንም ገድያለሁ ብሏል፡፡

የሮይተርስ የአይን እማኝ በፍንዳታው ቦታ ብትንትኑ በወጣው ሚኒባስ የአካላት ቁርጥራጮች መመልከቱን ተናግሯል፡፡

የሶማሊያ ጦር አዛዥነት ስልጣን በቅርቡ የተረከቡት ጄነራል ሞሀመድ አህመድ ጂማሌ በወታደራዊ አጀብ ይጓዙ ከነበሩ ባለስልጣናት አንዱ የነበሩ ቢሆንም ከጥቃቱ ተርፈዋል፡፡ምንጭ -www.DW.com