በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት ላይ ትኩረቱን ያደረገ የብሔራዊ ድህንነት ኮንፈረንስ በመጪው ግንቦት ወር በለንደን ሊካሄድ መሆኑ ተገለጸ ።
በኮንፈረንሱ ወቅት እንግሊዝ ለሶማሊያ የሚታደርገውን የ21 ሚሊዮን ዮሮ ድጋፍን ይፋ ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል ።
ከጥቂት ቀናት በፊት የሶማሊያ መንግስትና የሶማሊያ የፌደራል ክልሎች መካከል ታሪካዊ የሆነ የፖለቲካ ስምምነት ያደረጉ ሲሆን በስምምነቱ መሠረት የፌደራልና የክልል ኃይሎችን በማዋሃድና የአመራር ኃላፊነት በመሥጠት በአገሪቱ የተቀናጀ የብሔራዊ ደህንትን ለመፍጠር ታቅዷል ፡፡
በመጪው ግንቦት ወር በእንግሊዝ ለንደን ከተማ በሚደረገው ኮንፈረንስ የሶማሊያ ስምምነት ይበልጥ ተቀባይነትና እወቅና እንዲያገኝ እገዛ ይኖረዋል ።
በሶማሊያ የተቀናጀ የብሔራዊ የደህንነት እንዲኖር ለማስቻልና አቅምን ለመገንባት የእንግሊዝ መንግሥት ለሶማሊያና ለአፍሪካ ህብረት ሠራዊት ወታደራዊ ሥልጠናዎችን ለመሥጠት ቃል ገብቷል ።
በተጨማሪም እንግሊዝ ከሶማሊያ መንግሥት ጋር በመሆን በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እንዲሁም ሽብርተኝነት ለመዋጋት የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት እንደሚንቀሳቀስ ተመልክቷል ።
ሶማሊያ አዲስ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ካካሄደች በኋላ እኤአ በ2020 ሰላማዊና የበለጸገች ሶማሊያን ለመፍጠር የተሰነቀውን ራዕይ ለማሳካት በአገሪቱ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ማሻሻያዎችን በማድረግ ላይ ትገኛለች ።
በእንግሊዝ የሚደረገው ኮንፈረንስ የሶማሊያ ድርቅና ሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች አለም አቀፋዊ ምላሽ እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑ ተመልክቷል ፡፡
ሶማሊያ ከእ.አ.አ 2012 ጀምሮ በተለያዩ አገራት የፖለቲካ፣ የደህንነትና አለም አቀፋዊ ድጋፍ ሲደረግላት እንደነበረ ይታወቃል ፡፡