ለደቡብ ሱዳን ግጭት መባባስ ኡጋንዳና ኬንያ ምክንያት መሆናቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት አስታወቀ

ለደቡብ ሱዳን ግጭት መባባስ ኡጋንዳ እና ኬንያ ምክንያት እየሆኑ ነው ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወቀሰ፡፡ 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ሊያቆም ይገባል ሲል ከምንጊዜው በላይ ግፊቱን እያሳደረ ይገኛል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት መቀዛቀዙ ከየትኛውም ጊዜ በላይ አሳስቦኛልም ብሏል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከል ልዩ አማካሪ  አዳማ ዲየንግ ኬንያና ኡጋንዳ  ለደቡብ ሱዳን የሰላም እጦት መባባስ አሉታዊ አስተዋጽዎ እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡

አዳማ ዲየንግ ሰኞ ሰኞ ትኩረቱን በደቡብ ሱዳን  ባደረገው የሬድዮ ፕሮግራም ላይ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ህዝቦቹን ከሰላም እጦትና ችግር መከላከል ቅድሚያ ኃላፊነቱ የወደቀው በደቡብ ሱዳን መንግስት ላይ ቢሆንም ከዚህ ባለፈ ሸክሙ ወደ ጎረቤት አገራትና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ  ሊሻገር እንደሚገባ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል፡፡                 

የዋና ጸሓፊው የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከል ልዩ አማካሪው አዳማ ዲየንግ ኬንያን እና ኡጋንዳን የከሰሱበት ዋና ምክንያት በሁለቱ አገራት በኩል የጦር መሳሪያ በገፍ ወደ ደቡብ ሱዳን እየገባ መሆኑን መረጃዎች በማመላከታቸው ነው፡፡

በተለያየ ጎራ የተሰለፉ የደቡብ ሱዳን አንጃዎችን ወደ አንድ አገራዊ አጀንዳ ማምጣት ላይ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ግዴታውን በአፋጣኝ ሊወጣ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

ስለ የተባበሩት መንግስታት ክስ በዋሽግተን የሚገኙት የኬንያም ሆነ ኡጋንዳ ኢምባሲዎች ያሉት የለም፡፡

የአፍረካ ህብረት ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ መሀመት የደቡብ ሱዳን ሰላም እክል የሆኑ አካላት ላይ ማዕቀብ የሚጣልበት ግዜ አሁን ሲሉ በ30ኛው  የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ላይ ተደምጠዋል፡፡

አዳማ ዲየንግም ማዕቀብ እንዲጣል ይፈልጋሉ፡፡አለም አቀፉ እና የቀጠናው ማህበረሰብ ለተፋላሚዎች የድርድር መድረክ ከማመቻቸት ጀምሮ አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ ለመወስድ ዝግጅት ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡

ለደቡብ ሱዳን ሰላም መስፈን እየሰሩ ካሉ ጥምረቶ አንዱ የሆነው የምስቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንገስታት ኢጋድ አሁንም ከፈረንጆቹ የካቲት 5-16 ድረስ የሚቆይ የሰላም ምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ማዘጋጀቱ ታውቋል፡፡

አዳማ ዲየንግ ከዚህ በኋላ ጦርነት አማራጭ የሚሆንበት እድል ሊዘጋ ይገባል ብለዋል፡፡ኢጋድ የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ክፍተት ሊሞላ የሚችል እርምጃ ሊወስዱ ይገባል ሲሉ አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ላለፉት አራት አመታት በደቡብ ሱዳን ለታየው ኢ ሰብዓዊ ድርጊቶች የተፋላሚዎች ለሰላም መስፈን ፍላጎት ማጣት እና የሚደረሱ ስምምነቶችን ተግባራዊ አለማድረግ ዋንኞቹ ምክንያቶች ናቸው፡፡