ኤርትራና ሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በሚያጠናክሩበት ጉዳይ ላይ ስምምነት ላይ ደረሱ

ኤርትራና ሶማሊያ  ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን  በሚያጠናክሩበት ጉዳይ  ለይ  ከስምምነት  መድረሳቸው ተገለጸ ።

በሌላ በኩልም  የተባበሩት መንግሥታት  ድርጅት  የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ  ላይ ተጥሎ  የቆየው ማዕቀብ  በሚነሳበት  ሂደት ላይ ውይይት አድርጓል  ።

ኤርትራ እና ሶማሊያ ላለፉት አስራ አምስት ዓመታት የዘለቀ የዲፕሎማሲያዊ ግንኑነት አልነበራቸውም፡፡

አሁን ላይ ግን ይህ ተቀይሯል ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ላለፉት አስርት ዓመታት ከዘለቀው ሰላም አልባ ጦርነት በኋላ አዲስ በጀመሩት የሰላም ሂደት ቀጠናውም የሰላም አየርን እያስተናገደ ነው፡፡

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሙሀመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ወደ ኤርትራ ተጉዘው የሁለቱን ሀገራት ወደ ቀደመ ሰላም ለመመለስ  ፍሬያማ ስምምነት አድርገዋል፡፡

በአዲሱ የኤርትራ እና ሶማሊያ ስምምነት መሰረት ሁለቱ ሀገራት ለአስራ አምስት ዓመታት አቋርጠውት የነበረው የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዳግም ይመለሳል፡፡

ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የተደረገው የሰላም ስምምነት አሁን ወደ ሶማሊያ ዘልቆ ገብቷል፡፡

ይህ የሁለቱ ሀገራት የሰላም ግንኙነት የቀጠናውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ከማሳደጉ ባለፈ የንግድ መዳረሻ ማዕከል ለማድረግ አይነተኛ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

በዚህ ስምምነት መሰረት ሶማሊያና ኤርትራ አምባሳደሮቻቸውን በሁለቱ ሀገራት ዋና ከተማዎች መካከል እንዲያስቀምጡ እድል ይሰጣል፡፡

የፖለቲካ ተንታኝ የሆነው  አቡበከር አልባድሪ እንደሚለውየኤርትራ አዲሱ የዲፕሎማሲ ሂደት የአፍሪካ ቀንድ ቀጠናን ያጠናክራል ይላል፡፡

ኤርትራ ባለፉት ሃያ ዓመታት ከቀጠናው ሀገራት ጋር በነበነራት የሻከረ ግንኙነት ከጦርነት በዘለለ ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊ እና ስትራቴጅካዊ ግነኙነት በቀጠናው እንዲዳከም ሆኗል፡፡ ይህ ለቀጠናው አዲስ ምዕራፍ ነው ብሏል ።

የቀይ ባህር አካልላ የምትገኘው ኤርትራ ከኢትዮጵያ፣ጁቡቲና ሶማሊያ ጋ በድንበር ተዋሰናለች በተለይ ሀገሪቱ በሶማሊያ ለታጠቁ ኃይሎች ድጋፍ በማድረግ ቀጠናው ሰላም እንዳያገኝ እያደረገች ነው በሚል ከተባበሩት መንግስታት ድጅትም ማዕቀብ ተጥሎባት ቆይቷል፡፡

ይሁን እንጂ ኤርትራ ይህ ከአውነት የራቀ  መሆኑን ስታስተባብል ቆይታለች፡፡

ኤርትራ በሶማሊያ የታጠቁ ኃይሎችን ትደግፋለች በሚል ተወንጅላ ነበር፡፡ ይሁንና አሁን ላይ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ወደ ሀገሪቱ በመሂድ ጉብኝት ማድረጋቸው አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ በሁለቱ ሀገራት መካከል  ብቻ ሳይሆን በቀጠናውም መልካም ግንኙነት የሚፈጥር ነው፡፡

ከስምምነቱ በኋላ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሙሀመድ አብዱላሂ ፋርማጆ እንዳሉት ሀገራቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኤርትራ ላይ የጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ ትደግፋለች ብለዋል፡፡

እንደ ፕሬዝዳቱ በኤርትራ ላይ የተጣለው ማንኛውም የኢኮኖሚ ማዕቀብ እና እገዳ እንዲነሳ ሶማሊያ ትወተውታለች ብለዋል፡፡

ይህ የሚሆነውም በቀጠናው ያለውን ኢኮኖሚያዊ ውህደትን ለማጠናከር እንደሚጠቅም በመገንዘብ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ በሚነሳበት ሂደት እየመከረ መሆኑን የቻይናው ዓለምአቀፍ የቴሌቭዥን ኔትወርክ ዘግቧል፡፡

ፕሬዝዳት ሙሐመድ አብዱላሂም በኤርትራ የነበራቸውን የሶስት ቀናት ጉብኝት አጠናቀዋል፡፡