ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታና ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቀጠናዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ መከሩ

አሜሪካ ከኬኒያ ጋር በንግድ ግንኙነት ላይ አብሮ መስራት በሚቻልበት ጉዳዮች ላይ እየተነጋገረች ነው፡፡

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከኬኒያ ጋር ለማጠናከር የወጠኑት የንግድ ምጣነ ሃብታዊ ግንኙነት እየዳበረ የመጣውን የቻይና-አፍሪካ የንግድ እና ሌሎች ምጣነ ሃብታዊ ትስስርን ለመቀነስ ያለመ ስለ መሆኑ ግን ከወዲሁ እየተነገረለት ይገኛል፡፡

የኬኒያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ በዋሽንግተን ጉብኝት እያደረጉ ባሉበት ባሁን ወቅት ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ውይይት ሲያደርጉ አብይ ትኩረታቸውን በነግድ እና የጸጥታ ጉዳዮች ላይ አድርገዋል፡፡

ሚስተር ኡሁሩ ከዋሽንግተን ጋር በገቢያ እና ሌሎች ምጣነ ሃብታዊ ግንኙነቶች ስተሳሰሩ እምብዛም ዋጋ በማያስከፍል መልኩ መሆን እንዳለበት ይፈልጋሉ ነው የተባለው፡፡

ናይሮቢ ከቤጂንግ ጋር ባላት የጠበቀ ምጣነ ሃብታዊ ግንኙነት በኬኒያ በርካታ የንግድ እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች በቻይና መንግስት መገንባታቸው ይታወቃል፡፡ ኬኒያ ካሉባት የውጭ እዳ ክምችቶች 70 ከመቶውን የሚያጠቃልለው የቻይና መንግስት መሆኑም መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ባለፉት አስርት ዓመታት ከአፍሪካ ጋር የንግድ ግንኙነቷን አጠናክራ የያዘችው ቤጂንግ በምዕራባውያን በበላይነት ተይዞ የነበረውን በማዕድን የበለጸገውን የአፍሪካ የተፈጥሮ ጸጋን ኢኮኖሚያዊ አጠቃቀም ወደ መቆጣጠርም እየተሸጋገረች ትገኛለች፡፡

በዚህም ተግባሯ አፍሪካ ከአውሮፓ እና አሜሪካ ጋር የነበራትን የጠበቀ የንግድ ግንኙነት በመስበር የገበያ ቁጥጥሩን ወደ እጇ ለማስገባት ብዙ ርቀት ሄዳለች፡፡

በዚህም ንዴታቸውን ከመግለጽ የማይቆጠቡት የምዕራባውያን የፖሊቲካ ተንታኞች ቻይና በአፍሪካ እያሳደገች የመጣችውን ተጽዕኖ መቆጣጠር ካልተቻለ አውሮፓ እና አሜሪካ ከአፍሪካ ገበያ ውጭ መሆናቸው አይቀረ መሆኑን ያሳስባሉ፡፡

ቻይና ለኢንቨስትመንት እና ለኢኮኖሚዋ ጥቅም ብቻ ስትል በአፍሪካ በርካቶችን ታፈናቅላለች ለሰብአዊ መብቶች እና ዴሞክራሲ ግንባታም ስፍራ የላትም ሲሉም ይከሱአታል፡፡ በሌላ በኩል የአፍሪካ-ቻይና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነትን አፍሪካን ለመቀራመት ከሚደረገው ድርጊት ጋር የሚያገናኙ ተንታኞችም በአሸናፊነት እና ተሸናፊነት ጎራ በመፈረጅ በአሁን ወቅት ቻይና በዘርፉ የበላይነት መያዟን ያረጋግጣሉ፡፡

በአፍሪካ ቻይና በላቀ ደረጃ በኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ከተቆራኘችባቸው ሀገራት ደግሞ ኬኒያ በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች፡፡

ወደ ሃላፊነት ከመጡ ገና 2 ዓመታትን እንኳ ያላስቆጠሩ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በስልጣን ዘመናቸው መስራት ከሚፈልጉ ስራዎች አንዱ የአፍሪካ-አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ብሎም ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ማሻሻል እንደሚፈልጉ ገና ከጅምራቸውም መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡

ፕሬዝዳንት ትራምፕ የቻይና -አፍሪካን የወቅቱን ቁርኝት በመቀልበስ የምስራቅ አፍሪካ ሁነኛ የቻይና አጋር ከሆነች ኬኒያ ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቁርኝት ለማጠናከር መፈለጋቸውም ከዚሁ ውጥናቸው ጋር የሚያያዝ ነው የሚል መላምት እያሰጠባቸው ነው፡፡

እናም ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ከኬኒያ ጋር ልወያዩበት ከሚፈልጉ ቀጠናዊ የጸጥታ ጉዳዮች በተጨማሪ በአፍሪካ እያየለ የመጣውን የቻይና ተጽዕኖ መግታትን ውጥናቸው አድርገው በምጣነ ሃብታዊ ግንኙነቶች ላይ በማተኮር ከኬኒያው አቻቸው አሁሩ ኬኒያታ ጋር መክረዋል ሲል የዘገበው አልጀዚራ ነው፡፡