የኢጋድ ወታደራዊ መሪዎች በደቡብ ሱዳን ወቅታዊ የሰላም ሁኔታ ላይ መከሩ

የኢጋድ ወታደራዊ መሪዎች በደቡብ ሱዳን ወቅታዊ የሰላም ሁኔታ ላይ በካርቱም መምከራቸዉ ተገለጸ ።

መሪዎቹ የሀገሪቱን  አሁናዊ  የፀጥታና ደህንነት ሁኔታ በመገምገም በቀጣይ የኢጋድ ወታደራዊ  ኃይል በሀገሪቱ በሚሠማራበት አግባብ ላይ በስፋት መወያየታቸው ተነግሯል።

የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የልማት በይነ መንግስታት /ኢጋድ/ ወታደራዊ ባለስልጣናት ትላንት ሰኞ በሱዳን ካርቱም ባደረጉት ስብሰባ በወቅታዊ የደቡብ ሱዳን ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ በስፋት መምከራቸው ተነግሯል።

በቀጣይም የህብረቱ ወታደሮች ወደ ሀገሪቱ በሚዘምቱነትንና ከዚያ አስቀድመው መሥራት በሚገባቸው ቅድመ ተግባራት ላይም ጭምር ምክክር ተደርጓል።

ህብረቱ ባለፈው መስከረም ወር ላይ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳንና ኡጋንዳ በቀጣይ ወታደሮቻውን በደቡብ ሱዳን ያሰማራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

 ይህም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ከቀጠናዉ ሀገራት የሚወጣጡ 4 ሺህ ወታደሮችን በደቡብ ሱዳን ለማሠማራት ያቀደው ዉጥን አካል እንደሆነም ተሰምቷል።

ወታደሮቹ ቀድሞ በመንግስታቱ ድርጅት ጥላ ሥር በደቡብ ሱዳን ተሰማርተው የሚገኙ 13 ሺህ የመንግስታቱ ድርጅት የደቡብ ሱዳን ተልዕኮ ወታደሮችን የሚያግዙ ይሆናሉም ነው የተባለው።

በካርቱም ውይይት የኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ጂቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን እና ኡጋንዳ ወታደራዊ መሪዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ የአፍሪካ ህብረትን በሊቀ መንበርነት የምትመራዉ  ሩዋንዳ ተወካይም በውይይቱ መሳተፋቸው ተነግሯል።

ከውይይቱ መጠናቀቅ በኋላ የወጡ መረጃዎች እንዳመላከቱት ሀገራቱ ቀጠናዊ ወታደራዊ ኃይሉን ለማጠናከርና በወቅታዊ የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ሂደት ዙሪያ መጥብቅ ስለመምከራቸው ተገልጿል። 

ህብረቱ ከሁሉም አባል ሀገራት የተወጣጡ ወኪሎች የተካተቱበት ገምጋሚ ቡድን ያቋቋመ ሲሆን ቡድኑም የቀጠናውን ደህንነት ለመጠበቅ የተቋቋመው ወታደራዊ ኃይል አሁን ላይ ያለበትን ወቅታዊ አቋም በመገምገም በፈረንጆቹ ህዳር 19 በኢትዮጵያ በሚካሄደው የወታደራዊ መሪዎች ስብሰባ ላይ ሪፖርት እንዲያቀርብ ኃላፊነት ተሰጥቶታል።

በስብሰባዉ ላይ ንግግር ያደረጉት የሱዳኑ የመከላከያ ሚኒስትር አዋድ እብን ኦፍ በደቡብ ሱዳን ያለዉ የሰላም ሁኔታ ለቀጠናዉ ደህንነትም ወሳኝነት ያለዉ መሆኑን ተገንዝበው የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።

የደቡብ ሱዳኑ ወኪል በበኩላቸው በወቅታዊ የሀገራቸዉ የሰላምና መረጋት ሁኔታ ላይ ማብራሪያ  ሠጥተዋል ።

ደቡብ ሱዳን እኤአ 2011 ከሱዳን ተገንጥላ እንደ ሀገር ከቆመች 7 አመታት ያልዘለላት ብትሆንም ገና ከነፃነቷ ማግስት በ2013 በሀገሪቱ የተቀሰቀሰዉ የእርስ በእርስ ግጭት በርካቶችን ለሞት በሚሊየን የሚቆጠሩትን ደግሞ ለስደት መዳረጉ ይታወሳል።(ምንጭ: የሱዳን ትሪቡን)