ደቡብ ሱዳን የሰላም ቀን ልታከብር ነው

ደቡብ ሱዳን የሰላም ቀን ልታከብር እየተዘጋጀች መሆኑን አስታወቀች፡፡

ሀገሪቱ ቁኑን ለማክበር የወሰነችው የደቡብ ሱዳን  መንግስት ከተፋላሚዎቹ ጋር የሰላም ስምምነት መፈራረሙን ተከትሎ በሀገሪቱ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ተከትሎ ነው፡፡

እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር ከ2013 ጀምሮ በደቡብ ስዳን ሰማይ ስር ነግሶ የቆየው የእርስ በርስ ጦርነት ሳቢያ ከ400 ሺ በላይ የሀገሪቷ ዜጎች ለሞት የተዳረጉ ሲሆን ከ4 ሚሊዬን የሚልቁት ደግሞ ለስደት መዳረጋቸው የተለያዩ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ከሱዳን ተገንጥላ የዓለም አዲሷ ሀገር ከተባለች ከሁለት አመት በኋላ ወደ ግጭት የገባችው ሀገር ዛሬ ላይ ታሪኳን ለማደስ የተዘጋጀች መስላለች፡፡ ለዚህም አብይ ማሳያው ደግሞ ደቡብ ሱዳን የሰላም ቀንን ለማክበር ደፋ ቃና እያለች መሆኑ ነው፡፡

በደቡብ ሱዳን መንፈስ የጀመረውን የሰላም አየርን ለማወደስ የተዘጋጀውን ፕሮግራም እንዲታደሙ ሀገሪቷ ለወዳጆቿ ጥሪም አስተላልፋለች፡፡

ከአምስት ዓመታት የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲያበቃ እና ሀገሪቷ ወደ ሰላማዊ መንግስታዊ ስራ እንድትመለስ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ አታካቹን የዲፕሎማሲያዊ የድርድር ተግባር የደገፉ ሀገራት መሪዎች እና ተቋማትም በዚህ ቀን እንዲታደሙ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡

ለዚህም ደቡብ ሱዳን የአፍሪካ ሀገረት መሪዎች፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ኢጋድ ተወካዮችንና የተቃዋሚ መሪዎችን  ወደ ጁባ መጥራቷ ተሰምቷል፡፡

የመንግስትን ጥሪ ተቀብሎ የሀገሪቱ ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ዶክተር ሬክ ማቻርም ፕሮግራሙን ለመታደም ወደ ደቡብ ሱዳን እንደሚያቀና አስታውቋል፡፡

ይህ ደግሞ ሬክ ማቻር ምክትል ፕሬዝዳንትነቱን ትቶ በስደት ወደ ደቡብ አፍሪካ ካመራበት ከ2016 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የሀገሩን አፈር ይረግጣል ማለት ነው፡፡

የደቡብ ሱዳን መንግስት የሰላም ቀን ማክበር ያስፈለገው በሀገሪቱ የሰፈነው ሰላም ዘላቂ ይሆን ዘንድ በቁርጠኝነት እየሰራ እንዳለ ለደቡብ ሱዳናውያኑ ማረጋገጫ ለመስጠት መሆኑም ተመልክቷል፡፡

በሀገሪቱ የደህንነት ስጋትን ማስወገድ፣ የተቀናጀ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ማሻሻያዎችን ማከናወን እና የተዋሄደ መንግስትን መፍጠር አሁንም ለደቡብ ስዳን ሰላም ተግዳሮቶች መሆናቸው ቢቀጥልም ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ግን ይህንን ኩነት በእርግጥም ደቡብ ሱዳን ለሰላሙ በቁርጠኝነት እየሰራች ለመሆኗ ማሳያ አድርገውታል ሲል የዘገበው ሲጂቲኤን ነው፡፡