ደቡብ ሱዳን በሱዳን መንግስትና በሱዳን ታጣቂ ቡድኖች መካከል የሚደረገውን የሰላም ድርድር ልታስተናግድ ነው

ደቡብ ሱዳን በሱዳን መንግስትና በሱዳን ታጣቂ ቡድኖች መካከል የሚደረገውን የሰላም ድርድር ልታስተናግድ ነው፡፡

ለአመታት በእርስ በርሰ ግጭት ስትታመስ የቆየቸው ደቡብ ሱዳን በሱዳን አደራዳሪነት በመንግስትና በተቃዋሚዎች መካከል በካርቱም የተፈረመውን የሰላም ስምምት ተከትሎ ሀገሪቱ አንጻራዊ ሰላም የሰፈነባት ይመስላል፡፡

ይህንን ተከትሎ ደቡብ ሱዳን በሱዳን ስላም መሬት እንዲይዝ የራሷን ድርሻ ለመጫወት ወስናለች፡፡ ለራሷ ሰላም መስፈን አይነተኛ ድርሻ የተጫወተችውን የጎረቤቷን የሱዳንን ብድር ለመክፈል በሚመስል መልኩ ደፋ ቀና ማለት ጀምራለች፡፡

ከደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት የወጣው መረጃ ደቡብ ሱዳን የዳርፉር ንቅናቄ ቡድንን ጨምሮ በሱዳን የሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች ከሀገሪቱ መንግስት ጋር የሚያደርጉትን የሰላም ድርድር ለማስተናገድ እየተሰናዳች መሆኗን ያመላክታል፡፡

ባለፈው ሳምንት ደቡብ ሱዳን በአጎራባች ድንበሯ አካባቢ በሚገኙ ሁለት ቦታዎች በመጋጨታቸው ለሁለት የተከፈሉትን  የሱዳን ነጻነት ንቅናቄ ግንባር ዳግም ለማገናኘት እና ከካርቱም መንግስት ጋር ያለባቸውን ክፍተት ለመፍታት የሚያስችል የሽምግልና ሚና እንደምትጫወት ማስታወቋ አይዘነጋም፡፡

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት በብሉ ናይል፣ በደቡብ ኮርዶፋን እና በዳርፉር የሚገኙትን ጨምሮ ሁሉንም የሱዳን ታጣቂ ቡድኖች ጁባ በምታስተናግደው የሰላም ውይይት ላይ እንዲታደሙ ጥሪ ማቅረባቸውን የፕሬዝዳንት አማካሪ ቱት ኪው ጋት ሉአክ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡

አማካሪው የፕሬዝዳንቱን ጥሪ የሱዳን መንግስት እና ሁሉም የሀገሪቱ ታጣቂ ቡድኖች ተቀብለውታል ብለዋል፡፡

ጥሪ የተደረገላቸው የሱዳን ተቀናቃኝ ሀይሎች ጥሪውን ተቀብለው በሚቀጥለው ሳምንት በጁባ ለመወያየት ፍቃደኛ መሆናቸውን መግለጻቸውንም አስታውቀዋል፡፡

የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አል-በሽር ቀደም ሲል ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት የሱዳን መንግስትን እና ታጣቂ በድኖችን ለማሸማገል ያቀረቡትን ጥያቄ ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

ሆኖም ግን በደቡብ ሱዳን እና በደቡብ ሱዳን አማጺያን መካከል ሶስት ወራትን ያስቆጠረው የሰላም ውይይት በሱዳን አደራዳሪነት መካሄዱን ተከትሎ ሁለቱ ተጻራሪ ሀይሎች መስማማታቸው በሁለቱ ሱዳኖች መሪዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ተጠናክሯል፡፡

ጁባ ለማስተናገድ ደፋ ቀና እያለችለት ያለው የሰላም ሂደትም በሱዳን መንግስት እና በአማጽያን መካከል ያሉ ግጭቶችን ለማስቆም ይረዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የአፍሪካ ህብረት የሱዳንን ተጻራሪ ብድኖች ለማደራደር ሲያደርግ የነበረውን ጥረት ያግዛል ተብሏል፡፡ (ምንጭ፡-ሱዳን ትሪቡን)