የዩጋንዳ መንግሥት ለደቡብ ሱዳን መንግሥት የጦር መሣሪዎችን ሲያደርስ መቆየቱ ይፋ ተደረገ

የዩጋንዳ መንግስት አለምዓቀፉን የጦር መሳሪያዎች እገዳ በመጣስ ለደቡብ ሱዳን መንግስት የጦር መሳሪያዎችን ሲያደርስ መቆየቱን አንድ ጥናት ይፋ አድርጓል፡፡

አንድ መቶ አምስት ገጾች ያሉት የጥናት ሪፖርቱ ለደቡብ ሱዳን የተሸጡ መሳሪያዎችንና ጥይቶችን የሚያሳይ ማስረጃ መያዙም ተነግሯል፡፡

 በደቡብ ሱዳን ላይ ለረጅም ጊዜ ያስቆጠረ የጦር መሳሪያዎች ማዕቀብ ቢጣልም አሁንም ድረስ አዳዲስ የጦር መሳሪያዎች በጎረቤት ሀገራት በኩል በእርሰ በእርስ ግጭት ለቆየችው ደቡብ ሱዳን የጦርነት ቀጠናዎች ሲደርሱ መቆየታቸው ይነገራል፡፡

አራት አመታትን የፈጀውና መቀመጫውን እንግሊዝ ለንደን ባደረገው ለግጭቶች መንስኤ በሚሆኑ የጦር መሣሪያዎች ላይ ጥናት በሚያደርገው ተቋም ይፋ የሆነው መረጃ በተለይም በጎረቤት ሀገር ዩጋንዳ በኩል እየገባ ያለው የጦር መሳሪያ እንደአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ2013 የጀመረው የደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ግጭት እንዲባባስ ምክንያት ሆኖ መቆየቱን አመልክቷል፡፡

የዩጋንዳ መንግስትም አለማቀፉን የጦር መሳሪያዎች እገዳ በመጣስ ለደቡብ ሱዳን መንግስት የጦር መሳሪያዎችን ሲያደርስ መቆየቱንም ነው ጥናቱ ይፋ ያደረገው፡፡

አንድ መቶ አምስት ገጾች ያሉት ይኸው የጥናት ሪፖርት ለደቡብ ሱዳን የተሸጡ መሣሪያዎችንና ጥይቶችን የሚያሳይ ማስረጃ አያይዟል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እንደአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር ሀምሌ 2018 በደቡብ ሱዳን ላይ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ከማስተላለፉ በፊት የአውሮፓ ህብረት በአባል ሀገራቱ በኩል ለሱዳን የሚከናወን ማንኛውንም አይነት የጦር መሳሪያ ሽያጭ እ.ኤ.አ ከ1994 ጀምሮ አግዶ ነበር፡፡

ይህ ማዕቀብም እ.አ.ኤ በ2011 ከሱዳን በመገንጠል ነጻነቷን የተቀዳጀችውን ደቡብ ሱዳንን እንዲያካትት ውሳኔ ማስተላለፉ አይዘነጋም፡፡

ይሁን እንጂ ለሱዳን መንግስት ጦር አልፎ አልፎ ከአሜሪካና ከአውሮፓ ሀገራት የሚመጡ የጦር መሳሪያዎችን በዩጋንዳ በኩል ሲቀርብለት መቆየቱን ነው ጥናቱ ያመላከተው፡፡

ጥናቱ በዩጋንዳ በኩል ለደቡብ ሱዳን የጦር መሳሪያ ሲያቀርቡ የነበሩት የአውሮፓ ሀገራት ስሎቫኪያ ሮማኒያ እና ቡልጋሪያ ስለመሆናቸው ጥናቱ ያስቀምጣል፡፡

የተቃዋሚ ኃይሉ ግን የጦር መሣሪያዎችን በቀላሉ ማግኘት አለመቻሉን እና የወዳደቁ የጦር መሳሪያዎች ላይ ጥገኛ ለመሆን መገደዱንም ያሳያል፡፡

የደቡብ ሱዳን የኢንፎርሜሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ሚካኤል ማኩዬ የጥናቱ ውጤት ትክክል አለመሆኑንና መንግስታቸው እንደማይቀበለው ለአሶሼትድ ፕሬስ ገልጸዋል፡፡

በጊዜው ደቡብ ሱዳን የጦር መሳሪያ ለመግዛት ገንዘብ የላትም ነበር ያሉት ሚኒስትሩ ጁባ ደግሞ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ለማረጋገጥ ገንዘብ ትፈልጋለች ብለዋል፡፡ 

በያዝነው ወር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይፋ ያደረገው መረጃም ዩጋንዳ የጦር መሳሪያ እገዳውን በመተላለፍ ለደቡብ ሱዳን የጦር መሳሪያዎች ታቀርባለች በሚል መክሰሱ አይዘነጋም ሲል የዘገበው ዘ ገልፍ ቱደይ ነው፡፡