ደቡብ ሱዳንን ከድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ ፓርቲያቸው መዘጋጀቱን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማርዲያት አስታወቁ

ደቡብ ሱዳንን ከድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ ፓርቲያቸው መዘጋጀቱን የሱዳን ህዝብ ነፃነት ግንባር ፖርቲ ሊቀ መንበር እና የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማርዲያት አስታወቁ፡፡

ሀገሪቱን እየመራ ያለው የሱዳን ህዝብ ነፃነት ግንባር ፓርቲ አሁን ላይ በሀገሪቱ በጦርነት ምክንያት ወደ ኋላ የቀረችበት ልማት እንቅስቃሴን በመቀየር ኢኮኖሚዋን በማሳደግ ዜጎቿ ከክፉኛ ድህነት እንዲላቀቁ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲትም ከተቀናቃኝ የፖለቲካ ሀይሎች ጋር ስምምነት ከፈጠሩ በኋላ ፊታቸውን ደቡብ ሱዳን ከድህነት ወደ ምትወጣበት መንገድ ያቀኑ ይመስላሉ፡፡

በደቡብ ሱዳን አሁን ላይ ከ83 በመቶ በላይ ህዝቧ በገጠር የሚኖር እና መሰረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶችን እንኳን በወጉ የማያገኙ ዜጎች ያሉባት ሀገር ነች፡፡

በሀገሪቱ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ዜጎች ደግሞ በቀን እንኳን አንድ ዶላር ገቢ ማግኘት የማይችሉ እንደሆነ ጥናቶች ይተቁማሉ፡፡ ይህ አሀዝ ሀገሪቱ ክፉኛ በድህነት አረንቋ ውስጥ እንዳለች የሚያሳይ ነው፡፡

ፕሬዝዳንት ኪርም ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን ካገኘችበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን እስካለችበት ጊዜ ድረስ የድህነት መጠኗ ከ50.6 በበመቶ ወደ 83 በመቶ ከፍ ማለቱን በመግለፅ ይህንን አሀዝ ለመቀየር ትልቅ ስራ እንደሚጠብቃቸው ነው የገለፁት፡፡

ከአምስት አመታት የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ የሰላም ጭላንጭል እየታባት የሚገኘው ደቡብ ሱዳን በፖለቲካ ሀይሎች መካከል በወረደው ሰላም ስምምነት ሀገሪቱን ከድህነት ለማላቀቅ እንደማዕዘን ድንጋይ ሊንወስደው ይገባል ሲሉ ፕሬዝዳንት ኪር ለፓርቲያቸው አባላት ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ሱዳን ትልቁ ጠላት ድህነት ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ኪር ይህ ችግር በሀገሪቱ  የማሕይምነት፣ የጤና ቀውስ፣ የሙስና እና ብልሹ አሰራር ችግሮችን እንዲያሰራፉባት አድርጓል ብለዋል፡፡

በመሆኑም አሁን ላይ ደቡብ ሱዳን ከገባችበት የኢኮኖሚ ድቀት እንድትወጣ ለማስቻል ፓርቲያቸው ከመከፋፈል በመውጣት እና ጠቃሚ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን በመንደፍ በትኩረት እንደሚሰራ ነው የተናገሩት፡፡ (ምንጭ፡-ሱዳን ትሪቢዩን)