ጅቡቲ ለግብፅ አንድ ሚሊየን ስኩዌር ሜትር የእቃ ማቆያ ቦታ ፈቀደች

ጅቡቲ ለግብፅ አንድ ሚሊየን ስኩዌር ሜትር የእቃ ማቆያ ቦታ መፍቀዷን አስታወቀች፡፡

ጂቡቲ በቅርብ ጊዜያት የበርካታ ሃያላን ሃገራትን ቀልብ በመግዛት ከአሜሪካ እስከ ቻይና፣ ከፈረንሳይ እስከ ሩሲያ ያሉ እና ሌሎች ታላላቅ ሃገራት በምስራቅ አፍሪካ የጦር ጣቢያቸውን እንዲገነቡ ስትፈቅድ ቆይታለች፡፡

ከአረብ ሊግ ሃገራትም የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች እና ቱርክ በጂቡቲ ማረፊያ ካላቸው ሃገራት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

አሁን ደግሞ ሌላኛዋ የአረብ ሊግ አባል ሃገር ሰሜን አፍሪካዊቷ ግብጽ ከጂቡቲ ማረፊያ መሬት ማግኘቷ ነው የተሰማው፡፡

ግብፅ የአፍሪካ በርካታ አገራት የውጭ ንግድ መተላለፊያ በሆነችው ጅቡቲ በተሰጣት አንድ ሚሊየን ስኩዌር  ሜትር ወይም 247 ሄክታር ቦታ ላይ የእቃ ማቆያ ወይም ሎጂስቲክስ ዞን ለመገንባት እየተዘጋጀች መሆኑን የጅቡቲ አምባሳደር ሙሀመድ ዞህር ሀርሲ ተናግረዋል፡፡

አምባሳደሩ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነትን ለማጠማከር እየተሰራ መሆኑን ከሀገሪቱ ፓርላማ የአፍሪካ ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ ታሪቅ ሪድዋን  ጋር ባደረጉት ምክክር ነው የተናገሩት፡፡

አምባሳደር ሀርሲ በሁለቱ ሀገራት መካከል የጠነከረ ግንኙነት እንዲኖር እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች እንደማይጠፉ ግምታቸውን በማስቀመጥ የግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ይሰራሉ ሲሉም ተስፋቸውን ገልፀዋል፡፡
ግብጽ ባላት አለም አቀፍ አየር መንገድ  አፍሪካዊያን እንዲጠቀሙ እያደረገች ነው ያሉት የጅቡቲው አምባሳደር ጂቡቲ በዚህ ተጠቃሚ ልትሆን እንደምትችልም ነው የገለጹት፡፡

ግብጽ የፈረንጆቹ 2019 የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር መሆኗ ጅቡቲን ያስደሰተ እድል ነው ብለውታል፡፡

ግብፅ እና ጅቡቲ የኢኮኖሚ እና የንግድ ትስስር እንዳያደርጉ የትራንስፖርት ምቹ አለመሆን እንደምክንያት ይነሳል፡፡

ሁለቱ ሀገራት የቀጥታ  የአየርም ሆነ የባህር ትራንፖርት አለመጀመራቸውን ዘገባው አትቷል፡፡

ጅቡቲ ከዚህ ባሻገር ግብፅ በዩኒቨርሲቲ ትምህርት ያላትን ልምድ ትፈልጋለች፡፡

ስም ያላቸው የግብፅ ዩኒቨርሲቲዎች በጅቡቲ ቅርንጫፋቸውን እንዲከፍቱ  እንዲሁም በቅድመ ዩኒቨርሲቲ ትምርትም ግብፅ እርዳታ እንድታደርግ የጅቡቲ ባለስልጣናት ስለመጓጓታቸው ኢጂብት ቱዴይ ዘግቧል፡፡

ለዚሁ የሚረዳ መሬት ጅቡቲ በበቂ እንደምታዘጋጅ አምባሳደር ሀርሲ ተናግረዋል፡፡     

አምባሳደሩ ከኤርትራ ጋር የነበረው አለመግባባት መፈታቱን በመናገር የሁለትዮሽ ውይይት እየተደረገ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

የግብፅ ፓርላማ የአፍሪካ ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ ታሪቅ ሬድዋን ለአምባሳደሩ ከሀገራቸው ወሳኝ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር ስለ ሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መጠናከር እንደሚመክሩበት ቃል ገብተውላቸዋ፡፡

የሚመሩት ኮሚቴ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ ሀሳቦችን ጅቡቲ ባቀረበች ቁጥር በፓርላማው መወያያ እንዲሆን ያለተቃውሞ እንቀበላለን ነው ያሉት፡፡

በ2019 ግብፅ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር መሆኗን ለአፍሪካ አንድነት መጠናከር ትጠቀምበታለች ብለዋል ሬድዋን፡፡
 

ትብብር ለልማት በሚል መሪ ቃል እንደምትሰራ ነው የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ለኢጅብት ቱዴይ የተናገሩት፡፡ ግብጽ በተለያዩ ዘርፎች ያላትን የካበተ ልምድ ለአፍሪካዊያን ወንድሞቿ ታካፍላለችም ብለዋል፡፡