ፕሬዚደንት አልበሽር በሱዳን ተቃውሞ ከተቀሰቀሰ በኋላ የመጀመሪያ መልዕክታቸውን አስተላለፉ

በሱዳን ኑሮ ተወደደብን በሚል የተነሳው ተቃውሞ  የቀጠለ ሲሆን ፕሬዝደንት ኦማር ሃሰን አልበሽርም ተቃውሞ ከተቀሰቀሰ ወዲህ የመጀመሪያ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በሱዳን ላለፉት ስድስት ቀናት በኑሮ ተወደደብን በሚል በተለይም በዳቦ እና ነዳጅ እጥረት ምክንያት የተቀሰቀሰው አሁንም አለመብረዱ ነው የተነገረው፡፡

በሺዎች የሚቆጠሩ የሃገሪቱ ዜጎች በአደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን እየገለጹ ነው፡፡

ተቃውሞ በተለያዩ አካባቢዎች መቀጠሉን ተከትሎ ፖሊስ ተቃውሞውን ለመበተን ባደረገው ሙከራም ግጭት ተፈጥሮ በህይወትና በአካል ላይ ጉዳት መድረሱ ነው የሚነገረው፡፡

ተቃዋሚዎች በግጭቱ ምክንያት 22 ዜጎች ተገድለዋል ሲሉ መቀመጫውን ለንደን ያደረገው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽል በበኩሉ 37 ዜጎች በግጭቱ መሞታቸውን ገልጿል፡፡

የሃገሪቱ መንግስት ግን ሰልፈኞቹ ከፖሊስ ጋር ተጋጭተው 8 ሰዎች ተጎድተዋል ከማለት ውጭ የሞቱትን ይፋ አላደረገም፡፡

አሁን የሰልፈኞቹ መፈክር የዳቦና የነዳጅ ዋጋ እና እጥረቱ ይቀረፍ ኑሮ ተወደደብን የሚለው የተቀየረ ይመስላል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች በቤተ መንገስቱ አቅራቢያ አልቃሳር በተባለው መንገድ አካባቢ ተሰባስበው ነጻነት እንፈልጋለን፡ፍትህ እንፈልጋለን ፕሬዝደንቱ ከስልጣን ይውረዱ የሚሉ መፈክሮች አሰምተዋል ነው የተባለው፡፡

ፖሊስ ሰልፈኞችን ለመበተንም አስለቃሽ ጭስ መጠቀሙንና በርካታ ሰልፈኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ምንጮችን ጠቅሶ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

ፕሬዝደንት ኦማረ ሃሰን አልበሽር በሃገሪቱ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ አስመልክቶ ለመጀመሪ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክትም የተቃውሞ ሰልፉ በውጭ ሃገራት ጫና ምክንያት የተቀሰቀሰ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የሃገሪቱን የኢኮኖሚ ሁኔታ ለማሻሻልና የኑሮ ውድነቱን ለማረገብም መንግስት እየሰራ መሆኑን አስተላልፈዋል፡፡

አሜሪካና አንግሊዝን ጨምሮ ሌሎች የምዕራባውያን ሃገራት ከሰብዓዊ ጥሰትና ሙስና ጋር ተያይዞ በሱዳን ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ መጣላቸው ይታወሳል፡፡

ምንም እንኳ ፕሬዝደንት አልበሽር  ይህን ቢሉም የሃገሪቱ ተቃዋሚዎች ግን የተቃውሞ ሰልፍና የሃገሪቱን ችግር  ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ መሆኑን እየገለጹ ነው፡፡

የሱዳን ኮምኒስት ፓራቲው ሳዲቅ ካቢሎ እንደሚሉት የሃገሪቱ የኢኮኖሚ ችግር የሃገሪቱ ፖለቲካ መቀላቀል ያስከተለው ችግር መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡

የ74 አመቱ ፕሬዝደንት አልበሽር ላለፉት 3 አስርት አመታት አካባቢ ሱዳንን በፕሬዝደንት እየመሩ ሲሆን በመንግስታቸው ሰብዓዊ ጥሰትና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ተፈጽመዋል በሚል በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ እንደቆረጠባቸው ይታወቃል፡፡