አሜሪካ በአልሸባብ ላይ የምትወስደዉን እርምጃ አጠናክራ መቀጠሏን አስታወቀች

አሜሪካ በአልሻባብ ላይ የምትወስደውን እርምጃ አጠናክራ  መቀጠሏን አስታወቀች ።

የአሜሪካ ወታደር በወሰደው እርምጃ 52 የቡድኑ ተጣቂዎችን መግደል መቻሉ ይፋ አድርጓል፡፡ አሸባሪ ቡድኑ ሰፊውን የሀገሪቷን የገጠር ክፍሎች በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ ያለ ቢሆንም በዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ የሚፈፅማቸውን ጥቃቶች አቅዶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡

የአሜሪካ ጦር እኤአ በ2017 ጀምሮ ነው በሶማሊያ የመሸገውን የአልሸባብ ቡድን መዋጋት እንደጀመረ ይታወቃል፡፡

በእነዚህ ጊዜያቶችም 47 ያህል ጥቃቶችን መፈጸም የቻለ ሲሆን በርካታ የቡድኑ ተጣቂዎችን ሊገድል እንደቻለ ይገልጻል።

በስፍራው የሚገኘው የአሜሪካ ጦር አሸባሪ ቡድኑ ሞቃዲሾን ለቆ ከወጣ በኋላ ሰፊውን የሀገሪቷ የገጠር ክፍል በስፋት ተቆጣጥሮ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡ በተለይም የሀገሪቷን ደቡባዊ እና መካከለኛ ክፍል ተቆጣጥሮ የሚገኝ ሲሆን ከዛ በመነሳት ነው ጥቃት የሚፅመው፡፡

በሥፍራው ላይ ጥቃቶችን እየፈጸመ ያለው የአሜሪካ የቶር ክፍል በቡድኑ ላይ የሚወስዳቸውን አርምጃ መጠኑን በማስፋት እየሰራ ነው የሚገኘው፡፡

በዚህም ጥቃት የአሜሪካ ጦር በወሰደው የአየር ላይ ጥቃት ከ52 በላይ የቡድኑ አባላትን መግደል መቻሉን ነው አስታውቋል፡፡ በተወሰደው እርምጃ አልሸባብ ያለው ነገር ባይኖርም ራሱን ለመከላከል ያደረጋቸው ውግያዎች ከባድ እንደነበር የአሜሪካ አፍሪካ ኮማንድ ክፍል አስታውቋል፡፡

አሁድ እለት አሸባሪ ቡድኑ በኪስማዩ አካባቢ ባደረሰው ጥቃት ቁጥራቸው ከ10 ያላነሱ የሶማሊያ መንግስት ወታደሮች ሞተዋል፡፡

ቡድኑ በወቅቱ ጥቃት ለመፈፀም የተጠቀማቸው መሣሪያዎች ዘመናዊ እና ከባድ የሚባሉ በመሆናቸው በሰዓታት ውስጥ በሁለቱ ወታደሮች መካከል ማለትም በአሻባሪው ቡድን እና በሶማሊያ ወታደሮች መካከል በተደረገ ውጊያ የአሥር ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ በወቅቱ አልሸባብ ቡድኑ 15 የመንግስት ወታደሮችን መግደሉን ነው ያስታወቀው፡፡

የአሜሪካ የጦር ክፍል እንዳስታወቀው ቡድኑ በሶማሊያ ጠንካራ ይዞታ ያለው ሲሆን አሁድ እለት በመንግስት ወታደሮች ላይ ጥቃት ባደረሱ የአሸባሪ ቡድኑ አባላት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እንዳደረሰ ነው የገለፀው፡፡ በዚህም ጥቃት አንድም የንፁኋን ህይወት ያላለፈ መሆኑን አስታውሷል፡፡

ጥቃቱን ያደረሱት የአሸባሪ ቡድን የመንግስት ወታደሮች ካሉበት ጂሊብ ከምትባል ከሞቃዲሾ በ370 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ ከተማ ላይ ነው፡፡

ባለፈው የፈረንጆች 2018 ዓመት በሞቃዲሾ ከተማ ሞቃዲሾ ሆቴል ላይ በደረሰ የቦምብ ጥቃት ከ300 በላይ የሚሆኑ ንፁኋን ዜጎች ህይወት ሲያልፍ ጥቃቱን ያደረሰው የአሸባሪ ቡድኑ አባላት መገኛቸው እዚህ ቦታ እንደነበር ነው እርምጃውን የወሰደው የአሜሪካ የጦር ክፍል ያስታወቀው፡፡

በሶማሊያ ውስጥ ጠንካራ ይዞታ የነበረው አልሸባብ እኤአ ከ2011 ጀምሮ ሞቃዲሾን እየለቀቀ ይዞታውን ወደ ሌሎች የሀገሪቷ የገጠር ክፍሎች አድርጎታል፡፡

ይህም ደግሞ ቡድኑ የሚያደርሰው ጥቃት እንደድሮ ፈጣን ወታደራዊ እርምጃዎች ባይሆንም እየቆየ የሚያደርሳቸው ጥቃቶች ጉልብት እንዲኖረው አድረጎታል፡፡(ምንጭ:ሚድል ኢስት ሞኒተርና አልጀዚራ)