ሳውዲ ዓረቢያና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ለሱዳን የ3 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ሊያደርጉ ነው

የሳውዲ ዓረቢያና የተባበሩት አረብ ኢምሬት መንግስታት ለሱዳን የ3 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ሊያደርጉ ስለመሆኑ አስታወቁ፡፡

በሱዳን ከአምስት ወራት በፊት የዳቦ እና የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ምክንያት በርካታ ሱዳናውያን አደባባይ በመውጣት ባሰሙት ያልተቋረጠ ተቃውሞ  ጄነራል ኦማር ሐሰን አልበሽር ከስልጣን እንዲወርዱ ሆኗል፡፡

አሁን ሃገሪቱ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ መግባቷን ተከትሎ ሳውዲና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ከጎኗ ለመቆም ተዘጋጅተዋል፡፡ ሃገራቱ ለሱዳን የ3 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ወስነዋል፡፡

 

ሳውዲ ዓረቢያ ከምትሰጠው ድጋፍ ውስጥ 500 ሚሊዮን ዶላሩ በሱዳን ማእከላዊ ባንክ ተቀማጭ የሚሆን ሲሆን ይህ ደግሞ ሃገሪቱ ተጠባባቂ ገንዘብ እንዲኖራት የሚያግዝ እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡

የቀረው ገንዘብ ደግሞ ለሱዳን ሕዝብ ምግብን፣ መድሃኒቶችን እና የነዳጅ ወጪዎችን ለመደገፍ የሚውል መሆኑን ነው  ኤምሬትስ 24/7 የዘገበው፡፡

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በአፍሪካ ሀገራት ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች እየተንቀሳቀሱ ካሉት 17 ኩባንያዎች ጋር በመሆን ሱዳንን ለማልማት ከ7 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጪ አድርጋለች፡፡

ሱዳን ከሚያጋጥማት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ችግር እንድትላቀቅ በማሰብ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለሱዳን ማእከላዊ ባንክ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍም አድርጋለች፡፡

የአቡዳቢ ልማት ፈንድ በሱዳን ውስጥ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በበርካታ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ለሚንቀሳቀሱ 7 ነጥብ 3 ቢሊዮን ድርሃም ድጋፍ ማድረጉ ነው የተገለጸው፡፡

አቡዳቢ የልማት ፈንድ ለአፍሪካ ሀገራት እንደ መጓጓዣ፣ ሀይል፣ የውሃ እና የመስኖ ልማት በመሳሰሉ ቁልፍ የልማት ዘርፎች ለተሰማሩ  17 ፕሮጀክቶች 2 ቢሊዮን ድርሃም ድጋፍ ሰጥቷል፡፡

በተጨማሪም የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ እና የፋይናንስ እና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶችን ለመቀነስ የሚያስችለውን ገንዘብ ለሱዳን ማዕከላዊ ባንክ  5 ቢሊዮን ዶላር መስጠቱን ነው የተገለጸው፡፡

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በሱዳን የምታደርገው ኢንቨስትመንት በግምት 11 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል፡፡

ከዚህ ውስጥ የ5 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት በሂደት ላይ ሲሆን ቀሪዎቹ ገና ቅድመ-አፈፃፀም ደረጃ ላይ ናቸው፡፡