የሱዳን አደራዳሪዎች ሁለት የሽግግር ምክር ቤት እንዲቋቋም ሐሳብ አቀረቡ

የሱዳን ተቃዋሚዎችን እና ወታደራዊ ምክር ቤቱን እያደራደሩ የሚገኙት የሱዳን አደራዳሪዎች ሁለት የሽግግር ምክርቤት እንዲቋቋም ምክረ ሀሳብ ማቅረባቸው ተሰምቷል፡፡

በሱዳን በዳቦ እና ነዳጅ ዋጋ መናር ሳቢያ በተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ሀገሪቱን ለሶስት አስርተ አመታት የመሯት ጄነራል ኦማር ሀሰን አልበሽር ከስልጣን ተወግደው በምትኩ ወታደራዊው ምክርቤት ሀገሪቱን እያስተዳደረ ይገኛል፡፡

ይሁን እንጂ የሲቪል አሰተዳደር ካልተቋቋመ ቤታችን አንገባም ያሉ ተቃዋሚዎች  አሁንም አደባባዮችን የሙጥኝ እንዳሉ ይገኛሉ፡፡

ተቃዋሚዎቹን እና ወታደራዊ ሃይሉን የሚያደራድሩት አካላት አንድ በሲቪል አስተዳደር የሚመራ እና አንድ በወታደራዊ ሀይሉ የሚመራ ምክር ቤት እንዲኖር ምክረ ሀሰብ ማቅረባቸውን የሱዳን ነጻነት እና ለውጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት አመራር የሆነው ኦማር አልዲጌር ተናግሯል፡፡  

አልዲጌር አክሎም የሁለቱም ምክር ቤቶች ትክክለኛ የሥራ ድርሻ ገና አልተወሰነም ሲል ለአጃንስ ፍራንስ ፕረስ ተናግሯል፡፡

አደራዳሪዎቹ ያቀረቡትን የሁለት ምክርቤቶች ምክረ ሀሳብ ሁለቱም ወገኖች ስለመቀበላቸውም ሆነ ከዚህ ቀደም ተቃዋሚዎች ከሲቪል ማህበረሰቡ እና ከወታደራዊው አገዛዝ የተውጣጣ ምክር ቤት ይመስረት ሲሉ ባቀረቡት ሀሳብ ዙሪያ ስለመጽናታቸው ግልጽ የሆነ ነገር የለም ተብሏል፡፡

በጋራ ምክር ቤት ጥምረት ዙሪያ በሁለቱ ወገኖች  ልዩነቶች መፈጠራቸው ሲነገር የጦር አዛዦቹ በምክር ቤቱ ብዙኃኑን ወታደሮች እንዲካተቱ ሲሹ ተቃዋሚ መሪዎቹ ደግሞ ምክር ቤቱ በሲቪሎች እንዲመራ ይፈልጋሉም ነው የተባለው፡፡
አልበሽር ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ሀገሪቱን የማስተዳደር ሀላፊነትን የተረከበው ወታደራዊ ምክር ቤት ተነስቶ በሲቪል አስተዳደር ይተካ ያሉት አስር አባላት ያሉት በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች የወታደራዊው ምክር ቤት ዋና ቢሮ በሚገኝበት ካርቱም የበረሀው ሀሩር ሳይበግራቸው ደጅ ማደራቸውን እንደቀጠሉ ናቸው፡፡

ተቃዋሚዎች ይህንን ይበሉ እንጂ ወታደራዊ ምክር ቤቱ ግን ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳደር ለማስረከብ አሁንም አሻፈረኝ እንዳለ ነው፡፡

አደራዳሪዎቹ ከጋዜጠኞች፤ ነጋዴዎች እና ሌሎች ተጽእኖ ፈጣሪ ሙያዎች የተውጣጡ ናቸው ያለው አልዲጌር አደራዳሪዎቹ ሁለት  ምክር ቤቶች እንዲቋቋሙ ሀሳብ ከማቅረብም ባሻገር ከአልበሽር መወገድ በኋላ የተቋቋሙ የህግ አስፈጻሚ እና ህግ ተርጓሚ አካላት ስራቸውን በሚያከናውኑበት ሁኔታ ዙሪያም ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡

/ሲጂቲኤን/