የሱዳን ወታደራዊው የሽግግር ምክር ቤት በተቃዋሚዎች ላይ የማያዳግም ያለውን እርምጃ አዘዘ

ወታደራዊው የሱዳን የሽግግር ምክር ቤት በተቃዋሚዎች ላይ የማያዳግም ያለውን እርምጃ አዟል፡፡

የወታደራዊው የሽግግር ምክር ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው ለመገናኛ ብዙሃን ይፋ እዳደረጉት አንድ ቀን ብቻ በሚፈጀው የምርመራ ሂደት ተጠናቆ በስህተት ለጠፋው የሰው ህይወትም ሆነ ስለ ክስተቱ ሁሉም ነገር በእለተ ቅዳሜ ይፋ ይሆናል፡፡

የሱዳን የወቅቱ አስተዳዳሪ የሽግግር መንግስት ለመጀመሪያ ጊዜም ነው በካርቱም ባሉ የተቃዋሚዎች ቡድን ላይ በቀጥታ እንዲተኮስ በይፋ ያዘዘው ተብሎለታል፡፡

ውሳኔውን ተከትሎ የበርካቶች ህይወት ላይ የተላለፈ አደገኛ ውሳኔ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡

ይህን ተከትሎም የሱዳን ጉዳይ አሁን ላይ የዓለማቀፉ ማህበረሰብ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ወደ መሆን እየተሸጋገረ መሆኑ ተነግሮለታል፡፡

ሃገሪቱን ለገጠማት ቀውስ የመፍትሄ አቅጣጫ ለማፈላለግም አሜሪካ እና የአፍሪካ ህብረት መወጠናቸው እየተነገረ ነው፡፡

ከአንድ ቀን በፊት ለጋዜጠኞች ቃላቸውን ያሰሙት የወታደራዊ መንግስቱ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው ሻም አልዲን ካባሺ በካርቱም ያለውን የተቃዋሚዎች ስብስብ መበተን ተፈልጎ ነበር፡፡

የሱዳን ተቃዋሚዎች ግን የቀድሞ ፕሬዝዳንታቸው ኦማር ሃሰን አልበሽር በትረ ስልጣናቸውን ለቀው ዘብጥያ ከወረዱበት ከወርሃ ሚያዚያ ወዲህ የወታደራዊ ሃይል ዋና መስሪያ ቤትን ጨምሮ የመዲናዋ አደባባዮች የሙጥኝ እንዳሉ ናቸው፡፡

የተቃዋሚዎቹ ውጥን በሃገሪቱ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ይመሰረት ዘንድ ወታደራዊው የሽግግር መንግስት ስልጣኑን ለሲቪል ዜጎች ሊያስረክብ ይገባል የሚለው ነጥብ ዋነኛው ነው፡፡

ከ10 ቀናት በፊት በተቃዋሚዎች እና ወታደራዊው የሽግግር መንግስት መሃል ሲደረግ የነበረው ድርድር መቋረጡን ተከትሎ ቢያንስ 120 ሱዳናዊያን መቀጠፋቸውን የሱዳን ዶክተሮች ማህበር ይፋ አድርጓል፡፡

40 አስክሬኖች ከናይል ወንዝ ዳርቻ መሰብሰቡንም የአልጀዚራ መረጃ በዚሁ ላይ አክሏል፡፡

የአሁኑ የአድማ ብተኛ ትዕዛዝን ተከትሎ የጠፋው የሰው ህይትን አስመልክቶም ቃል አቀባዩ ካባሺ "ኮማንደሮች የተቃውሞ ሰልፉን እንዲበትኑ ታዘው ነበር፡፡ ያንንም ፈጽመውታል ግን ያልተፈለገ ስህተት በመፈጠሩ የሰው ህይወት ተከፈለበት” በማለት የስህተቱን ዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡

ካባሺ ለድርድሩ መቋረጥም ተቃዋሚዎችን ተወቃሽ አድርገዋል፡፡ ድርድሩን ያዘገየውን ነጥብም ሲያነሱ ተቃዋሚዎቹ የተሳሳተ ግንዛቤ መያዛቸውን ያወሳሉ፡፡ ሲቪል መንንግስት ተብሎ ቢጮህም ያለሂደት የሚሆን ነገር የለም ሲሉ የመንግስትን አቋም ይፋ አደረጉ፡፡

በሽግግር መንግስት ላይ የመፈንቅለ መንግስት እርምጃ ለመውሰድ መወጠኑንም ያወሱት ቃል አቀባዩ በ2 ቡድኖች የሚመራ ጥረት ግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር በማዋል መክሸፉን ጠቁመዋል፡፡

ካርቱም አሁን ላይ በከፋ የኢኮኖሚ ቀውስም ተመታ ትገኛለች፡፡ የአፍሪካ ህብረትም ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ለሱዳን አንዳች መፍትሔ እንዲያመጣ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

የአሜሪካ መልዕክተኞችም በሳውድ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶችና ግብጽ በካርቱም የተጠራውን ውይይት ሊቀላቀሉ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

ከቀድሞው ፕሬዝዳንት አልበሽር ስንብት ማግስት ሳውዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች 3 ቢሊየን ዶላር መለገሳቸው አይዘነጋም፡፡