በሱዳን የሲቪል አመራሮች አብላጫውን ቦታ የሚይዙበት መንግስት እንዲመሰረት ያለመ የድርድር ሃሳብ ቀረበ

ኢትዮጵያና የአፍሪካ ህብረት ለሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች አዲስ የድርድር ሀሳብ ማቅረባቸዉ ተነገረ። አዲሱ እቅድ የሲቪል አመራሮች አብላጫዉን ቦታ የሚይዙበት መንግስት እንዲመሰረት ያለመ በመሆኑ ወታደራዊ መንግስቱን ሲቃወሙ ለነበሩት ተቃዋሚ ኃይሎች አስደሳች ነዉ ተብሏል።

አገሪቱን ለ30 አመታት የመሯት ኦማር አልበሽር ከተወገዱ በኋላ ወታደራዊ መንግስት ሀገሪቱን መቆጣጠሩ ምቾት የነሳቸዉ ሱዳናዊያን የሲቪል መንግስት ስልጣን እንዲይዝ በብርቱ መጠየቃቸዉን ቀጥለዋል።

በሀገሪቱ የተከሰተዉን ፖለቲካዊ ቀዉስ ተከትሎም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ተፋላሚ ኃይሎች ችግራቸዉን በንግግር እንዲፈቱ ለማስቻል ጥረቶችን በማድረግ ላይ መሆናቸዉ ይታወሳል። የአፍሪካ ህብረትም ቢሆን ሱዳናዊያን ለችግራቸዉ በጠረጴዛ ዙሪያ ቢመክሩ ይበጃቸዋል ሲል ጠንካራ ምክረ ሀሳብ አቅርቧል።

ሆኖም ወታደራዊ መንግስቱም ሆነ ተፋላሚ ኃይሎች በቀረበላቸዉ የሰላም መንገድ ለመጓዝ የሄዱት ርቀት እምብዛም አይደለም። በዚህም ዛሬም በሱዳን ምድር ዘላቂ መረጋጋት ሊመጣ አልቻለም።

ታዲያ የሀገሪቱ ቀጣይ እጣ ፈንታ እንደነ የመንና ሶርያ እንዳይሆን ስጋት የገባቸዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድና የአፍሪካ ህበረት አዲስ የድርድር ሃሳብ ለሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ማቅረባቸዉ ተነግሯል።

ወታደራዊ መንግስቱ ስልጣኑን ለሲቪል መንግስት እንዲያስረክብ የሚጠይቁት ኃይሎች ትላንት ይፋ ያደረጉት መረጃ እንዳመላከተዉ ኢትዮጵያና የአፍሪካ ህብረት በሱዳን ያለዉን ችግር ለመቅረፍ ያለመ አዲስ የድርድር ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል።

አዲስ የቀረበዉ ምክረ ሀሳብ በአብላጫዉ የሲቪል መሪዎች የተካተቱበት የሽግግር መንግስት በሱዳን እንዲመሰረት የሚጠይቅ በመሆኑ የሱዳን ተቃዋሚዎችን ያስደሰተ ቢሆንም፣ አዲስ የሚመሰረተዉ መንግስት በምን መልኩ እንደሚዋቀር ግን ዝርዝር ጉዳዮች አለመታወቃቸዉ ተገልጿል።  

አዲሱ ምክረ ሀሳብ የሱዳን ወታደራዊ ጀነራሎች ኢትዮጵያና የአፍሪካ ህብረት በሱዳን የሽግግር መንግስት አወቃቀር ዙሪያ አዲስና አካታች የሆነ ምክረ ሀሳብ እንዲያቀርቡ መጠየቃቸዉን ተከትሎ የመጣ ስለመሆኑ ታዉቋል።

በአዲሱ እቅድ መሰረት ለሶስት አመታት የሚዘልቅ 15 አባላት ያሉትና በአብላጫዉ የሲቪል መሪዎች የተካተቱበት የሽግግር መንግስት የሚዋቀር ይሆናል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የህግ አዉጪ አካላት አወቃቀር ምን እንደሚመስል የታወቀ ነገር የለም።

ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ በቀረበዉ የድርድር ሃሳብ መሰረት 300 አባላት ያለዉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲዋቀርና ከዚህ ዉስጥም 67 በመቶ የሚሆኑት የምክር ቤቱ አባላት የወታደራዊ መንግስቱን ከሚቃወሙት የነፃነትና ለዉጥ ጥምረት እንዲካተቱ ያለመ ነበር።

ቀሪዉ 33 በመቶ ደግሞ ከቀድሞዉ ፕሬዝዳንት አልበሽር ናሽናል ኮንግሬስ ፓርቲ ዉጪ ያሉ ሌሎች ተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎች እንዲካትት ያቀደ ነበር።

ይህን በኢትዮጵያ የቀረበዉን ምክረ ሀሳብ የተቃዋሚ ኃይሎች ቢቀበሉትም ወታደራዊ አስተዳደሩ በእቅዱ ላይ ቅሬታ እንዳለዉ በመግለፁ አዲስ ምክረ ሀሳብ ማቅረብ ግድ ብሏል። በእርግጥ አዲሱን ምክረ ሀሳብ የሱዳን ተፋላሚዎች ይቀበሉት አይቀበሉት እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

እስካሁን በሱዳን በተቀሰቀሰዉ ህዝባዊ ተቃዉሞ ቢያንስ የ128 ዜጎች ህይወት ማለፉ ይነገራል ሲል አልጀዚራ ዘግቧል።