የሱዳን ተቃውሞ የሰዎች ህይወት መቅጠፉን ቀጥሏል ተባለ

የሱዳን ዜጎች በወታደራዊ መንግስቱ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ለግልጽ አሁንም ወደ ዋና ዋና መንገዶች የወጡ ሲሆን የሰው ህይወት መጥፋቱና ብዙዎች ላይ ጉዳት ስለመድረሱ እየተዘገበ ነው።

የሃገሪቱ የዜና ወኪል ከጤና ሚኒስትር መስሪያ ቤት አገኘሁት ብሎ ባወጣው መረጃ መሰረት ሰባት ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ 180 ደግሞ ጉዳት ደርወሶባቸዋል።

የተቃውሚ ኃይሎቹን የሚደግፈው የሱዳን ዶክተሮች ማዕከላዊ ኮሚቴ ግን ቢያንስ አምስት ሰዎች ስለመሞታቸው ገልጾ ነበር። በወርሃ ሚያዝያ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር በወታደሮች ከስልጣን ከተወገዱ ጀምሮ ሱዳን መረጋጋገት እርቋታል ነው የተባለው።

በያዝነው ወር በአስርታት የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ከተገደሉ በኋላ እስካሁን የእሁዱ ተቃውሞ ትልቁ ነው እየተባለ ነው።

ምንም እንኳን ከፍተኛ ወታደራዊ ቁጥጥር ቢኖርም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስቱ ስልጣን በሲቪል ለሚመራ ቡድን እንዲያስተላልፍ እየጠየቁ ነው።

የሱዳን ዶክተሮች ማዕከላዊ ኮሚቴ እንደገለጸው በኦምዱርማን አራት ሰዎች መገደላቸውንና አንድ ተቃዋሚ ደግሞ በአትባራ ከተማ ደረቱ ላይ በጥይት ተመትቶ መሞቱን ጠቅሷል።

የሽግግር ወታደራዊ ካውንስሉ ምክትል ሃላፊ ጄነራል ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ''በሰዎች ላይ ጉዳት እያደረሱ ያሉ አልሞ ተኳሾች አሉ፤ የፈጥኖ ደራሽ ወታደራዊ ቡድን ሶስት አባላትም ተመትተዋል፤ ስድስት ንጹሃን ዜጎችም ባልታወቁ ሰዎች ጥቃት ተሰንዝሮባቸዋል። እነዚህ ሰርጎ ገቦች ናቸው፤ ለውጡን ለማደናቀፍ እየሞከሩ ነው።'' ብለዋል።

ኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደዘገበው በፕሬዝዳንታዊ ቤተመንግስት አካባቢና ሌሎች ሶስት ግዛቶች የተሰበሰቡ ሰልፈኞችን ለመበተን የጸጥታ ሃይሎች አስለቃሽ ጭስ ተጠቅመዋል።

በኡምዱርማንና በጋዳሪፍ ከተማም አስለቃሽ ጭስ ስለመተኮሱ እየተዘገበ ነው። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)