ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በኬንያ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ነው

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በኬንያ ለሚያደርጉትን የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት በኬንያ  ናይሮቢ እያደረጉ ነው፡፡

ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር  ናይሮቢ  ሲደርሱም የኬንያ አቻቸው ኡሁሩ ኬንያታ ደማቅ አቀባበል እንዳደረጋቸውና ለክብራቸው ሲባልም 21 ጊዜ መድፍ የተተኮሰላቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡

ሳልቫ ኪር በኬንያ በሚኖራቸው የሁለት ቀናት የስራ ጉብኝትም ከፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር በደቡብ ሱዳን የሰላም ጉዳይ ዙሪያ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህ ባለፈም ፕሬዚዳንቶቹ በሀገራቱ መካከል ባለውና በቀጣይነት በሚኖረው  የንግድ ግንኙነት ዙሪያ ይወያያሉ ነው የተባለው።

ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በያዝነው ወር መጀመሪያ አካባቢ በናይሮቢ በተካሄደው 17ኛው ብሔራዊ የፀሎት መርሃ ግብር ላይ ከፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር መሳተፋቸው ይታወሳል።

ደቡብ ሱዳን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠርከ 2013 ጀምሮ በሀገሪቱ በተከሰተው የእርስ በእርስ ግጭት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለህልፈት የተዳረጉ ሲሆን፥ በሚሊየን የሚቆጠሩት ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

የእርስ በእርስ ግጭቱን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታትና የሀገሪቱን ሰላም ለማረጋገጥም ኢትዮጵያና ኬንያ መንግስታና ተቃዋሚ ሃይሎችን የማሸማገል ሂደቱን እያከናወኑ ይገኛሉ።

(ምንጭ፡-ቢቢሲ)