ኤርትራና ሱዳን የተዘጉ ድንበሮቻቸውን ለመክፈት ተስማሙ

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ምክትል ሃላፊ ሌተናል ጀኔራል ሞሃመድ ሃምዳን ደገሎ አስመራ ውስጥ ተገናኝተው ተወያይተዋል።

ውይይታቸውን ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት የመተላለፊያ ድንበሮች እንዲከፈቱ መስማማታቸው ተነግሯል።

ሱዳን በህገወጥ የሰዎች ዝውውርና ሌሎች ድርጊቶች ምክንያት በ2018 ድነበሯን መዝጋቷ ይታወሳል።

የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በትዊተር ባሰፈሩት መረጃ ሁለቱ ወገኖች በሀገራቱ የግንኙነት ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል ነው ያሉት።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ እና ሌተናል ጀኔራል ሞሃመድ ሃምዳን የተስማሙባቸውን ጉዳዮች የሚከታተል ጥምር ኮሚቴ እንደሚቋቋም አቶ የማነ በመረጃቸው አካትተዋል።

ከወራት በፊት ከስልጣን በወረዱት ኦማር ሀሰን አልበሺር የፕሬዚዳንትነት ዘመን ሱዳንና ኤርትራ መልካም የሚባል ግንኙነት እንዳልነበራቸው መረጃዎች ያሳያሉ ዘገባዉ የቢቢሲ ነዉ።