የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር መንግሥት የፖለቲካ እስረኞችን ለመልቀቅ ተስማማ

የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር መንግሥትና ተቃዋሚዎች እያደረጉ ባሉት ድርድር የፓለቲካ እስረኞችን ለመፍታት ስምምነት ላይ መድረሱን አሸማጋዮች ተናግረዋል።

አገሪቱን በሽግግር ወቅት ማስተዳደር ያለበት የትኛው አካል ነው? የሚለው ላይ ስምምነት ላይ መድረስ ስላልተቻለ የወታደራዊው ኃይልና የተቃዋሚዎች ድርድር እስካሁን ፍሬያማ መሆን አልቻለም።

የአፍሪካ ኅብረትና የኢትዮጵያ አሸማጋዮች ሁለቱ ኃይሎች ስልጣን መጋራት በሚችሉበት ነጥብ ላይ ከስምምነት ይደርሳሉ ብለው ተስፋ ያደርጋሉ። ሁለቱ ወገኖች ዳግመኛ ድርድር መጀመራቸው የሲቪል የሽግግር መንግሥት ለመመስረት ተስፋ እንደፈነጠቀም ይታመናል።

ድርድሮች ተቋርጠው ትናንት እንደ አዲስ በጀመሩበት ወቅት የአፍሪካ ኅብረት አሸማጋዮች ጊዜያዊ ወታደራዊ የሽግግር መንግሥቱ የፖለቲካ እስረኞችን ለመፍታት መስማማቱን ገልጸዋል። አሸማጋዮቹ የፖለቲካ እስረኞቹ የሚለቀቁበትን መንገድና ብዛት ላይ ያሉት ነገር የለም።

ሱዳንን እያስተዳደረ የሚገኘው ወታደራዊው ካውንስል ስልጣኑን ለሲቪል መንግሥት አሳልፎ እንዲሰጥ ዓለም አቀፍ ጫናዎች እየበረታበት ነው።

እሁድ ዕለትም በሽግግር መንግሥቱ ላይ ጫና ለመፍጠር በመላው አገሪቱ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል። ምንም እንኳ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ለእስር እየተዳረጉና ለወራት የኢንተርኔት አገልግሎት ቢቋረጥም የተቃውሞ ድምጻቸውን ለማሰማት አደባባይ ከመውጣት አላገዳቸውም። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)