ግብጽ የአፍሪካ ሀገራት የሚገጥማቸውን ችግሮች ለመሻገር በሚያደርጉት ጥረት ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች፡፡
የግብጹ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታ አልሲሲ በአፍሪካ አህጉር የሚገኙ ሀገራት የሚገጥማቸውን ማንኛውም ተግዳሮት ለማሻገር በሚያደረጉት ጥረት አስፈላጊውን ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀ መንበር የሆኑት አልሲሲ አፍሪካ በፖለቲካ፣ በጸጥታ እና በምጣኔ ሀብት ረገድ የሚገጥማትን ፈተና ለመሻገር አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ በግብጽ በኩል ዝግጁነት እንዳለ አስረድተዋል፡፡
አልሲሲ ከታንዛኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ካሲም ማጅሊዋ ጋር በነበራቸው ቆይታ በአፍሪካ ህብረት አማካይነት አማራጭ ስልቶችን ቀይሶ ችግሮችን መጋፈጥ የወደ ፊት እርምጃ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ካታንዛኒያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በነበራቸው ውይይት ሀገራቱ በትብብር ለመስራት በሚያስችላቸው አግባቦች ላይ መምከራቸው ታውቋል፡፡
በሂደቱም በሁለንተናዊ ረገድ የሚደረገው ትስስር በልማትና በተለያዩ ፕሮጀክቶች መታገዝ እንዳለበት አስምረውበታል፡፡ የታንዛኒያ ዲፕሎማቲክ ልኡኩ የስዊዝ ቦይ መተላለፊያን የገበኘ ሲሆን፣ ግብጽ አዲስ ለመገንባት የያዘቸው የዋና መዲና ግንባታ ሜጋ ፕሮጀክት ያለበትን ደረጃ ተመልክተዋል፡፡
ግብጽና ታንዛኒያ ለ55 አመታት የዘለቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፣ በንግድ ልውውጥ፣ በመሰረተ ልማት ዝርጋታና በተለያዩ ዘርፎች ጥብቅ ቁርኝት እንዳላቸው ይነገራል፡፡ የግብጽ ኩባኒያዎች በታንዛኒያ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን በመገንባት ተሳትፎ እያደረጉ ነው፡፡
ፕሬዝዳንት አልሲሲ በአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ለተፈረመው የነጻ ንግድ ልውውጥ ስምምነት መጽደቅ ላሳዩት የመሪነት ሚና ከታንዛኒያ ዲፕሎማሲዊ ልኡክ አድናቆት ተችሯቸዋል ሲል የዘገበው አህራም ኦንላይን ነው፡፡