ሱዳናውያን የዜጎች በወታደር መገደልን ተከትሎ ምሽቱን በተቃውሞ አሳልፈዋል ተባለ

ሱዳናውያን የዜጎች በወታደር መገደልን ተከትሎ ምሽቱን በተቃውሞ ማሳለፋቸው ተገለጸ፡፡

የሃገሪቱ ፖሊስም ተቃውሞ የነበረበትን አካባቢ ዘግቷል ተብሏል፡፡

ሰባት ወራትን ያስቆጠረው የሱዳናውያን ተቃውሞ አሁንም ቀጥሎ የዜጎቹን ህይወት እያስገበረ ነው፡፡

ቀድሞ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር ስልጣን ይልቀቁ፤ አሁን ደግሞ ሱዳንን ህዝባዊ መንግስት እንጂ ወታደራዊ መንግስት ሊመራት አይገባም በሚል ጠንከር ያለ ተቃውሞ እያካሄዱ ያሉት ሱዳናውያን የመጀመሪያ ጥያቄአቸው ምላሽ ቢያገኝም አሁንም ህዝባዊ መንግስት ስልጣን ባለመያዙ ተቃውሟቸው እልባት አላገኘም፡፡

በተለያዩ መንገዶች ተቃውሟቸውን እየገለፁ ያሉት ሱዳናውያኑ ምንም እንኳን በወኪሎቻቸው በኩል ውይይት ቢያደርጉም የዜጎቻቸውን ህይወት ከመቅጠፍ እና የከፋ ጉዳት ከማስከተል አላዳናቸውም ፤ ተቃውሟቸውም አላባራም፡፡

ትናንት ማምሻውም ተቃውሞው በተወለደባት ቡሪ በምትባል የካርቱም ምስራቃዊ ወረዳ ላይ በርካታ ሱዳናውያን ተቃውሟቸውን ሲገልፁ እንደነበር አልጀዚራ አስነብቧል፡፡

ተቃውሞው የተነሳው በካርቱም ደቡብ ምስራቅ በኩል በምትገኘው ኢል ሶክ በተባለች ከተማ ከሰዓታት በፊት ግድያ መፈፀሙን ተከትሎ መሆኑን ነው አልጀዚራ ምንጮቹን ጠቅሶ የዘገበው፡፡

ኢል ሶክ በተባለችው ከተማ ግጭት ሊነሳ የቻለው በከተማዋ በርከት ያሉ ወታደሮች በመኖራቸው እና ነዋሪዎችም ወታደሮቹ ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ በመጠየቃቸው ተኩስ ስለተከፈተባቸው ነው ተብሏል፡፡

ባለፉት ሶስት ቀናት ስድስት ንፁሃን ዜጎች መገደላቸውን እና የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ሃላፊነቱን ሊወስድ እንደሚገባ የሱዳን የዶክተሮች ማእከላዊ ኮሚቴ በትዊተር አስነብቧል፡፡

ከትናንት ምሽቱ ተቃውሞ ቀደም ብሎም 200 ሱዳናውያን ተቃዋሚዎች ‹‹ ህዝባዊ መንግስት፣ ህዝባዊ መንግስት›› በማለት ተቃውሟቸውን ሲገልፁ መቆየታቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል፡፡