የሱዳን ወታደራዊ ምክርቤት እና የተቃዋሚዎች ጥምረት ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ ላይ ከስምምነት መድረሳቸው ተነገረ

የሱዳን ወታደራዊ ምክርቤት እና የተቃዋሚዎች ጥምረት ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ ላይ ከስምምነት መድረሳቸው ተነገረ

ሱዳንን እያስተዳደረ ያለው ወታደራዊ ምክር ቤትና ዋነኛው የተቃዋሚዎች ጥምረት በሀገሪቱ የሽግግር መንግሥት ለመመስረት በር ይከፍታል በተባለለት ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ ላይ ከስምምነት ደርሰዋል ተብሏል።

ፕሬዝዳንት ኦማር አል በሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ መረጋጋት የተሳናት ሱዳን፤ወታደራዊው ምክር ቤት ስልጣኑን ከተቆናጠጠ በኋላም የሲቪል መንግስት ይመስረት በሚል ተቃዋሚዎች ድምጻቸውን ሲያሰሙ በመቆየታቸው መረጋጋት ተስኗት ቆይቷል።

በዚህም ምክንያት አገሪቷን እያስተዳደረ ያለው ወታደራዊ ምክር ቤቱና ዋነኛው የተቃዋሚዎች ጥምረት ከስምምነት ለመድረስ በርካታ ውይይቶችን ቢያደርጉም ሳይሳካ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

አሁን ግን ሁለቱ ሐይሎች የሽግግር መንግሥት ለመመስረት በር ይከፍታል በተባለለት ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ ላይ ከስምምነት ደርሰዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት አደራዳሪው ሞሀመድ ሀሰን ሌባት ስምምነቱን ይፋ ያደረጉ ሲሆን፤ ነገር ግን ዝርዝር ጉዳዮችን ከመግለጽ ተቆጥበዋል ተብሏል፡፡

በሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌው ላይ እየተካሄደ የነበረው ድርድር በመራዘሙ በሀገሪቱ የተከሰተው ግጭት መቋጫ እንዲያጣ አድርጎት መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፤ ሲጠበቅ የነበረው ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌው ላይ ከስምምነት መደረሱ እንደተሰማም የሱዳን ጎዳናዎች ደስታቸውን በሚገልጹ ዜጎች መሞላቱ ተዘግቧል።

ሰነዱ ባለፈው ወር በወታደራዊ ምክርቤቱና በተቋዋሚዎች መካከል የሶስት አመት የሽግግር መንግስት ለመመስረት የተቀመጠውን ስምምነት ይዘረዝራል፡፡ዘገባው የቢቢሲ ነው።