የመንግስታቱ ድርጅት ለሱዳን ህዝብ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላለፈ

በሱዳን ህዝባዊ መንግስት እንዲመሰረት መደላድል የሚፈጥር ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጽሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ለአገሪቱ ህዝብ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሱዳን የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ያደረገ ስምምነት መፈረሙን አስመልክቶ የድጋፍ መግለጫ አውጥቷል፡፡

በዚህም የሱዳን ህዝብን የቆየ የዲሞክራሲና የሰላም ምኞት ለማሳካት ብሎም የአገሪቱን የሽግግር ጊዜ ለመደገፍ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቁርጠኛ መሆኑን የተቋሙ ዋና ጽሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንዲያገግም በማድረግ ዘላቂ ልማት ለማምጣት ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በሱዳን ወታደራዊ ምክር ቤትና በተቃዋሚ ሀይሎች መካል የተፈረመው የስምምነት ሰነድ ሁለቱ ኃይሎች ስልጣን በመጋራት የሽግግር መንግስት መመስረት የሚያስችላቸው ነው፡፡

ስምምነቱ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ በተገኙበት ትላንት በካርቱም መፈረሙ ይታወቃል፡፡ (ምንጭ፦ ሽንዋ)