የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት የውጭ ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አወገዙ

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ በሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ዜጎች ንብረት ላይ የተፈጸመው ዝርፊያና ጥቃትን እንደሚያወግዙት አስታወቁ።

ማክሰኞ ዕለት ፕሬዝዳንቱ ''ለተፈጸመው ነገር ምንም አይነት ምክንያት ሊቀመጥለት አይችልም፤ ደቡብ አፍሪካውያን ሌሎች አፍሪካውያንን ማጥቃት አይችሉም'' ሲሉ ተደምጠዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም ከአርባ በላይ ደቡብ አፍሪካውያን ከሰኞ አመሻሽ ጀምሮ በቁጥጥር ስር ውለዋል። ፖሊስ አመጸኞቹን ለመቆጣጠር አስለቃሽ ጭስ የተጠቀመ ሲሆን፣ ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ መሆን ሲጀምሩ ደግሞ የጎማ ጥይቶችንም ጭምር ተጠቅሞ ነበር ተብሏል።

እስካሁን ቢያንስ አምስት ሰዎች መሞታቸውም ተሰምቷል።

''የተፈጸመው ዝርፊያ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የሌለው ነው፤ ይህ ነገር ደቡብ አፍሪካ ውስጥ እንዲሆን አንፈቅድም'' ብለዋል ፕሬዝዳንቱ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት የቪዲዮ መልእክት።

አክለውም ''ድርጊቱ በአስቸኳይ መቆም አለበት'' ብለዋል።

በሌላ በኩል የአፍሪካ ህብረት በበኩሉ፣ ተቀባይነት የሌለው ድርጊት ያለውን ተግባር በእጅጉ እንደሚቃወመው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ዝርፊያውና አመጹ ማክሰኞ ዕለትም የቀጠለ ሲሆን፣ አሌክሳንድሪያ ወደተባለችው ጆሃንስበርግ ክፍል መስፋፋቱ ተሰምቷል። አንዳንድ ነዋሪዎችም በሕገ-ወጥ መንገድ ወደሃገራችን የገቡ ስደተኞችን መንግስት ያባርርልን ሲሉ ቁጣቸውን ገልጸዋል።

ብዙ ጥቃት የደረሰባቸው ናይጄሪያውያን እንደመሆናቸው በናይጄሪያዋ ሌጎች ከተማ የሚገኙ የደቡብ አፍሪካዊያን ሱፐርማርኬቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው አንድ አይን እማኝ ለቢቢሲ አረጋግጧል።

አንድ ሌላ የአይን እማኝ ደግሞ ሱፐርማርኬቱ የሚገኝበት መንገድ ላይ የሁለት ሰዎች ሬሳ መመልከቱን ገልጿል።

የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሞሃሙዱ ቡሃሪ በበኩላቸው፣ የሀገራቸውን ቁጣ ለመግለጽና የዜጎቻቸውን ደህንነት ለማረጋገጥ ማክሰኞ ዕለት የልዑካን ቡድን ወደ ደቡብ አፍሪካ መላካቸውን አስታውቀዋል።

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲም ጉዳዩ እስኪጣራና ዝርፊያዎቹ እስከሚቆሙ ድረስ ዜጎች ሱቆቻቸውን እንዲዘጉ አሳስቧል። አመጽ ሊነሳባቸው ከሚችልባቸው ቦታዎች እራሳቸውን እንደያርቁና ውድ የሆኑ ጌጣጌጦችን እንዳያደርጉም አስጠንቅቋል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)