የአፍሪካ ህብረት በሱዳን የህበረቱ አባልነት ላይ ጥሎት የነበረውን እገዳ ማንሳቱን አስታወቀ

የአፍሪካ ህብረት በሱዳን የህበረቱ አባልነት ላይ ጥሎት የነበረውን እገዳ ማንሳቱን አስታወቀ፡፡

የአፍሪካ ህብረት የሱዳን ወታደራዊ ሽግግር ምክር ቤት ስልጣኑን ለሲቪል ማጋራት አለበት በሚል በሳለፍነው የአውሮፓዊያኑ ሰኔ ወር ከህብረቱ አባልነት ማገዱ የሚታወስ ነው፡፡.

የህብረቱ የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት በትላትናው እለት በአዲስ አበባ ባካሄደው ስብሰባ በሱዳን አሁን ላይ እየታየ ያለውን ለውጥ ተከትሎ አገዳውን ማንሳቱን ይፋ አድርጓል፡፡

ህብረቱ እገዳውን በጣለበት ወቅት የህብረቱ የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ በሀገሪቱ ያለው የስልጣን ሽግግር ሁሉን አሳታፊና ሙያዊ ምክክር እንዲካሄድበት የመፍትሄ ሀሳብ አቅርቦ እንደነበር ይታወቃል፡

ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤቱ ስልጣኑን ለሲቪሎች አሳልፎ እንዲሰጥ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ግፊት ሲደረግ ከቆየ በኋላ ከወታደራዊ ሽግግር ምክር ቤቱ እና ከሲቢሎች የተውጣጣ ሉዓላዊ ምክር ቤት ተቋቁሟዋል፡፡

በዚሁ ምክር ቤት በጠቅላይ ሚኒስተርነት የተሰየሙት አብደላ ሃማዶክ አዲሱን ካቢኒያቸውን በዚህ ሳምንት ማቋቋማቸው ይታወቃል፡፡፡፡

ለበርካታ ወራቶች በሱዳን በተካሄደው ተቃውሞ ሀገሪቱን ለ30 አመታት ያስተዳደሯት ኦማር ሀሰን አል በሽር ከስልጣን መነሳቸው የሚታወስ ነው። (ምንጭ፡-ሲጂቲኤን)