ናይጄሪያ 600 ዜጎቿን ከደቡብ አፍሪካ ልታስወጣ ነው

ናይጄሪያ በደቡብ አፍሪካ እየደረሰ ያለውን መጤ ጠል ጥቃት ተከትሎ 600 ዜጎቿን ልታስወጣ መሆኗን አስታወቀች።

ሁለቱ ሀገራት እየደረሰ ያለውን ጥቃት ተከትሎ ውጥረት ውስጥ መግባታቸው ይታወሳል።

የተወሰኑ ናይጄሪያውያን ረቡዕ ዕለት በሁለት አውሮፕላን እንደሚወጡ በጆሀንስበርግ የሚገኘው የናይጄሪያ ቆንጽላ ቢሮ ለቢቢሲ አስታውቋል።

ባለፈው ሳምንት በከተማዋ የውጪ ሀገራት ዜጎች የንግድ ተቋማት ላይ በደቦ በተፈፀመ ጥቃት አስር ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን፣ ከሟቾቹ መካከል ሁለቱ የውጪ ዜጎች መሆናቸው ታውቋል።

ጥቃቱ የተጀመረው የዕቃ ጫኝ መኪና አሽከርካሪዎች ከሌላ ሀገራት የመጡ ግለሰቦች ስራችንን እየነጠቁ ነው በሚል የስራ ማቆም አድማ ካደረጉ በኋላ ነው።

ደቡብ አፍሪካ ባላት የስራ እድል የተነሳ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በርካታ ወጣቶች የሚፈልሱባት ሀገር ናት።

ምንም እንኳ የሀገሪቱ ምጣኔ ኃብት ቢያድግም በደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ የሆነ የሥራ አጥ ቁጥር አለ፤ ለዚህም አንዳንድ የሀገሪቱ ዜጎች ከሌላ ሀገር የመጡ ግለሰቦች ሥራቸውን እየነጠቋቸው እንደሆነ ያስባሉ።

የናይጄሪያ ቆንፅላ ጄነራል ጎድዊን አዳማ እንዳሉት ከሆነ በመጤ ጠል ጥቃቱ የተነሳ ስጋት የገባቸውና ሀገሪቱን ለቅቀው መሄድ የሚፈልጉ ብቻ እንደሚሄዱ ተናግረዋል።

በዚህ መካከል የናይጄሪያ ዲያስፖራ ኮሚሽን አቢኬ ዳቢሪ ከደቡብ አፍሪካ ለሚወጡ ዜጎች መንግሥታቸው የገንዘብ ድጋፍ እንደማያደርግ አስታውቀዋል።

አቡጃ ውስጥ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ ናይጄሪያ የደቡብ አፍሪካ መንግሥትን ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚሠራ ገልጸው ለተጎጂዎች ካሳ መክፈልም አለበት ብለዋል።

በጆሀንስበርግ እሁድ እለትም ሌላ ግጭት ተቀስቅሶ የነበረ ሲሆን፣ ለግጭቱ መቀስቀስ ምክንያት የነበረው የተቃዋሚ ፓርቲው መሪ ያደረጉት ንግግር ነው ተብሏል።

በግጭቱ ወቅት መኪኖች ተሰባብረዋል ህንፃዎች ላይ ጥቃት ደርሷል። የደቡብ አፍሪካውያን ንብረት የሆኑ ሱቆችም ላይ ውድመት መድረሱ ተገልጿል።

ከዚህ ቀደም ብሎ "መጤዎች ወደ መጣችሁበት ሂዱ" የሚል መፈክር የያዙ ሠልኞች እየዘመሩ ሰልፍ ማድረጋቸውንና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ንግግር ወደሚያደርጉበት ስፍራ ማምራታቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኀን ዘግበዋል።

ጥቃቱን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ያወገዙት ሲሆን ሚሊዮኖች ደቡብ አፍሪካውያን በሚኖሩባት ከተማ ሥርዓት አልበኝነት እንዲሰፍን እንደማይፈቅዱ ተናግረዋል።

አክለውም በሀገሪቱ የሚገኙ የሌላ ሀገራት ዜጎች አብዛኞቹ ሕግ አክብረው የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ባለፈው ሳምንት የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ሙሐመዱ ቡሀሪ ናይጄሪያውያን በደቡብ አፍሪካ እየደረሰባቸው ባለው እንግልትና ጥቃት የተፈጠረባቸውን ቅሬታ ለመግለጥ የልዑካን ቡድን ልከዋል።

ከፕሬዝዳንቱ የወጣው መግለጫ እንደሚያሳየው የደቡብ አፍሪካ መንግስት ተጨባጭ እርምጃ በመውሰድ አፍሪካውያን ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት እንዲያስቆም ይጠይቃል።

ባለፈው ሳምንት የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ 420 ነውጠኞችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የገለጸ ሲሆን፣ ከእሁዱ ግጭት ጋርም በተያያዘ 16 ሰዎች መያዛቸውን አስታውቋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡