ግብፅ ከሱዳን ጋር ያላትን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማጠናከር እንደምትፈልግ ፕሬዚዳንት አል ሲሲ ገለጹ

ግብፅ ከሱዳን ጋር ያላትን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማጠናከር እንደምትፈልግ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ገለጹ፡፡

የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት በትናንትናው ዕለት ግብፅ ካይሮ የገቡ ሲሆን፣ ከግብጹ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ጋር በሀገራቱ የሁለትዮሽና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ሀገራቱ  በተለያዩ ዘርፎች ዙሪያ ያላቸውን ግንኙነት በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል መስማማታቸውን የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስማን አብደላህ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም መሪዎቹ በቀጠናው ስላለው የጸጥታ ሁኔታ፣ ሱዳን አሸባሪዎችን ከሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ በምትወጣበት ሁኔታ እና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አድርገዋል።

ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ግብፅ የቅርብ ጎረቤት ሀገር ከሆነቸው ሱዳን ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ቃል ገብተዋል።

በዚህም በአሁኑ ወቅት በሱዳን ያለውን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠልና በቀጠናው የሚስተዋለውን የሽብር ጥቃት በጋራ ለመከላከል ከሱዳን ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

ሀገራቱ በግብርና፣ በኤሌክትሪክ ሃይል፣ በመሰረት ልማት ግንባታ እና በሌሎች ዘርፎች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ያላቸውን ስምምነት ወደ ተግባር ለመቀየርም ቀጣይ ውይይቶች የሚደረጉ እንደሆነ የሱዳን ትሪቡን ዘገባ ያመለክታል፡፡