ግብፃውያን ፕሬዝዳንት አል-ሲሲን በመቃወም ሰልፍ ወጡ

ግብፃውያን ፕሬዝዳንት አል-ሲሲን በመቃወም ሰልፍ መውጣታቸው ተዘገበ፡፡

ሰልፉ፤ ፕሬዘዳንት አብዱል ፈታህ አል-ሲሲ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በግብፅ በተካሄደው የመጀመሪያ የተቃውሞ ሰልፍ ሲሆን፣ ፖሊስ ሰልፈኞችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ መጠቀሙ ተገልጿል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ግብፃውያን በታህሪር አደባባይ ሰልፍ ወጥተው፤ ፕሬዝዳንት አል-ሲሲ ሥልጣን እንዲለቁ ጠይቀዋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2011ዱ ተቃውሞ ማዕከል ከነበረው ታህሪር አደባባይ በተጨማሪ በሌሎች አካባቢዎችም ሰላማዊ ሰልፍ ተደርጓል ነው የተባው።

በተለያዩ አካባቢዎች ሰላማዊ ሰልፍ የተካሄደው የአል-ሲሲ ሙስና መወንጀላቸውን ተከትሎ ነበር።

ግብፃዊው ተዋናይና የቢዝነስ ሰው ሞሀመድ አሊ፤ አል-ሲሲ በቅንጡ ቤቶችና ሆቴሎች ላይ በርካታ ገንዘብ እያባከኑ እንደሚገኙ በመግለጽ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ቪድዮዎች አሰራጭቷል።

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ግብፃውያን በድህነት እየማቀቁ ሳለ ፕሬዝዳንቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እያባከኑ መሆኑንም ተናግሯል።

አል-ሲሲ የተባለው ነገር "ውሸት እና የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው" ሲሉ ውንጀላውን አጣጥለዋል።

ትላንት በትዊተር ላይ በስፋት ሲሰራጩ የነበሩ መልዕክቶች ሕዝቡ አል-ሲሲ ከሥልጣን እንዲነሱ እንደሚፈልግ የሚጠቁሙ ነበሩ።

አል ጀዚራ እንደዘገበው፤ በአሌክሳንድርያ እና ሱዌዝ ከተሞችም ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል።

ስፔን ውስጥ በስደት የሚኖረው ግብፃዊው ተዋናይና የቢዝነስ ሰው ሞሀመድ አሊ፤ የመጀመሪያ ቪድዮውን የለቀቀው መስከረም ሁለት ነበር። ፕሬዝዳንቱ ከሥልጣን የሚወርዱበት ቀነ ገደብ አስቀምጦ፤ አል-ሲሲ በተባለው እለት ከሥልጣን ካልወረዱ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚካሄድ ገልጾም ነበር።

ሞሀመድ ባስቀመጠው ቀነ ገደብ መሰረት፤ አል-ሲሲ ከሥልጣናቸው አለመነሳታቸውን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ግብፃውያን ሰልፍ ወጥተዋል።

ግብፅ ነጻነቷን ከተቀዳጀች በኋላ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት የሆኑት ሞሀመድ ሙርሲን በማስወገድ አል-ሲሲ ስልጣን የጨበጡት 2013 ላይ እንደነበር ይታወሳል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መታሰራቸውን በማጣቀስ፤ የአል-ሲሲን አስተዳደር በጽኑ ይተቻሉ።

2018 ላይ በተካሄደው ምርጫ አል-ሲሲ ጠንካራ ተቀናቃኝ ሳይኖር 97 በመቶ ድምፅ በማግኘት አሸንፈዋል። አል-ሲሲ እስከ 2030 ስልጣን ላይ እንዲቆዩ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ የማድረግ ሀሳብ አብላጫ ድምፅ ማግኘቱም ይታወሳል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)