አልሲሲን ለመቃወም አደባባይ የወጡ ግብፃውያን መታሰራቸው ተገለጸ

በመንግሥት የሚፈፀምን ሙስና ተቃውመው አደባባይ ከወጡ ግብፃውያን መካከል 500 ያህሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ተናገሩ።

የተቃውሞ ሠልፎቹ በካይሮ፣ አሌክሳንድሪያ እና ሌሎች ከተሞች አርብ ማታ የተካሄዱ ሲሆን፤ በወደብ ከተማዋ ስዊዝ ደግሞ ቅዳሜ ምሽት ተከናውኗል።

የመንግሥት ባለስልጣናት የታሳሪዎቹን ቁጥር እስካሁን ድረስ አልገለፁም።

የፕሬዝዳንት አብደል ፈታህ አልሲሲ አገዛዝ ተቃውመውት አልያም ተችተውት ድምፃቸውን በሚያሰሙ፣ ሠልፍ በሚያደርጉ ላይ እርምጃ በመውሰድ ይታወቃል።

እኤአ ከ2013 ጀምሮ አልሲሲ በሕዝብ የተመረጡት ሙርሲን በወታደራዊ ኃይል ከስልጣን ካወረዱ በኋላ፤ በሕዝብ መሰብሰቢያ ስፍራዎች ከ10 ሰው በላይ ሆኖ መገኘት የተከለከለ ሆኖ ቆይቷል።

የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት፤ ባለፉት ስድስት አመታት ከ60 ሺህ ግብፃውያን በላይ የሙርሲ ደጋፊ ናችሁ፣ አልያም በሕግ የታገደው የሙስሊም ወንድማማቾች አባል ናችሁ በሚል በእስር ቤት የሚገኙ ሲሆን፤ የተወሰኑት በፍርድ ቤት ሞት ተፈርዶባቸዋል። የደረሱበት የማይታወቅ ግለሰቦችም አሉ ብለዋል።

አርብ ምሽት በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በዋና ከተማዋ ካይሮ ታሕሪር አደባባይ አቅራቢያ፣ አሌክሳንድሪያ፣ ዳሚታ እና ማሀላ አልኩብራ በሚባሉ ስፍራዎች ሠልፍ ማድረጋቸውን የአይን ምስክሮች እና ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀን ዘግበዋል።

ተቃዋሚ ሠልፈኞቹን ፖሊስ ከመበተኑ በፊት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው "አልሲሲ ይውረድ" እንዲሁም "ሕዝቡ ሥርዓቱ እንዲፈርስ ይፈልጋል" እያሉ ሲጮሁ እንደነበር ተዘግቧል።

አንድ የሕግ ባለሙያ ለቢቢሲ 500 ያህል ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረው፤ በሚቀጥሉት ቀናትም ይህ ቁጥር እያሻቀበ እንደሚሄድ ያላቸውን እምነት አስረድተዋል።

መንግስታዊ ያልሆነው የግብፅ ምጣኔ ኃብትና ማኅበራዊ መብት ማዕከልም የታሳሪዎች ቁጥር 516 እንደሆነ ተናግሯል።

በቁጥጥር ስር የዋሉት በሕግ በታገደ ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ፣ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀን ሐሰተኛ መረጃ በማሰራጨት፣ ያልተፈቀደ ሰልፍ ላይ በመሳተፍና በሌሎች ወንጀሎች ተጠያቂ ይሆናሉ ተብሏል።

ከታሰሩት መካከል እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆነም ይገኝበታል ነው የተባለው፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል ታዋቂ የሰብዓዊ መብት ጠበቃዋ ማሄኑር አል ማስሪ ትገኝበታለች። እንደ ፈረንሳዩ የዜና ወኪል ከሆነ ጠበቃዋ በቁጥጥር ስር የዋለችው ቅዳሜ እለት ካይሮ ወደሚገኘው አቃቤ ሕግ ቢሮ የታሰሩ ሰዎችን በመወከል ከሄደች በኋላ ነው።

በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያሉ መገናኛ ብዙኀን፤ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀን ሠልፍ ተደረገ ተብለው የሚሰራጩ ምስሎች በ2011 የተካሄደው ሠልፍ ምስሎች መሆናቸውን በመጥቀስ ሕዝቡን ለማወናበድ ሆን ተብለው የተደረጉ ሲል ገልጿቸዋል።

በመላው ዓለም ኢንተርኔትን የሚከታተለው ኔት ብሎክስ የተባለው ድርጅት በበኩሉ፤ ቅዳሜ ግብፅ ውስጥ የፌስቡክ መልዕክት መቀበያና መላኪያ፣ ቢቢሲ እና ሌሎች የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀን ሰርቨሮች እቀባ ተጥሎባቸው ነበር ብሏል።

በግብፅ ተቃዋሚ ሠልፈኞች አደባባይ የወጡት በስፔን በስደት ላይ የሚገኘው ባለሀብት በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀን ላይ ፕሬዝዳንት አልሲሲንና ወታደራዊ ባለስልጣናትን በሙስና የሚከስ ተንቀሳቃሽ ምስል ከለቀቀ በኋላ ነው።

ይህ ግለሰብ ግብፃውያን ፕሬዝዳንት አልሲሲ ከስልጣን እንዲወርዱ ለመጠየቅ አርብ ዕለት ሕዝባዊ ሰልፍ እንዲወጡ ጠርቶ ነበር።

ፕሬዝዳንት አል ሲሲ የግለሰቡን ክስ "ሐሰተኛና ስም ማጥፋት ነው"ሲሉ አጣጥለውታል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)