ኢቦላ ወደ ኡጋንዳ እየተዛመተ ነው

በኡጋንዳ አንድ የአምስት ዓመት ህፃን በኢቦላ መያዙ መረጋገጡን የአለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።

ባለፉት አስር ወራት በዲሞክራቲክ ኮንጎ ብቻ 2ሺህ ታማሚዎች የተመዘገቡ ሲሆን የበርካቶቹ ጤና በአሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

አሁን በኡጋንዳ የታመመው ሕፃን ቅዳሜ እለት ከቤተሰቡ ጋር በመሆን ከኮንጎ ወደ ኡጋንዳ በድንብር በኩል የተሻገረ ነው።

የኡጋንዳ ባለስልጣናት እንዳስታወቁት ሕፃኑ ደም የቀላቀለ ማስመለስና ሌሎች ምልክቶችን እንዳሳየ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።

በልጁ ደም ውስጥ የኢቦላ ቫይረስ መገኘቱ የታወቀው በኡጋንዳ የቫይረስ ምርመራ ተቋም ውስጥ ምርመራ ከተደረገለት በኋላ ነው።

ወዲያው የዓለም ጤና ድርጅትና የኡጋንዳ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር የአስቸኳይ ጊዜ የሕክምና ቡድን ወደ ስፍራው የላኩ ሲሆን ቡድኑ ሌሎች ሰዎች በቫይረሱ መያዝ አለመያዛቸውን በመለየት አስፈላጊውን ሕክምናና ትምህርት ይሰጣል ብለዋል።

የኡጋንዳ ጤና ሚኒስትር ለመገናኛ ብዙኀን እንደገለፁት የህፃኑ ቤተሰቦችና ሌሎች የኢቦላ ምልክት የሚመስል የታየባቸው ሁለት ሰዎች ክትትል እየተደረገላቸው ነው።

ሚኒስትሯ በቲውተር ገጻቸው ላይ እንዳስቀመጡት ኡጋንዳ በአሁኑ ሰአት የኢቦላን ወረርሽኝ ለመከላከል በተጠንቀቅ ላይ ትገኛለች ብለዋል።

ኡጋንዳ ከ4 ሺህ 500 በላይ ጤና ባለሙያዎችን የኢቦላ መከላከያ ክትባት መስጠቷን የዓለም ጤና ድርጅትና የኡጋንዳ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር በጋራ በሰጡት መግለጫ ላይ አስታውቀዋል።

በኮንጎ የደረሰው የኢቦላ ወረርሽኝ በታሪክ ሁለተኛው ነው የተባለ ሲሆን በየሳምንቱ አዳዲስ በሽተኞች በከፍተኛ ቁጥር እየተመዘገቡ ነው ተብሏል።

ከባለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮ 1400 ሰዎች በኢቦላ ምክንያት መሞታቸው ታውቋል።/ቢቢሲ/