የመሐመድ ሙርሲ ስርዓተ ቀብር ተፈፀመ

የቀድሞ የግብጽ ፕሬዝዳንት መሐመድ ሙርሲ ስርዓተ ቀብር ተፈፀሟል፡፡

የሙርሲን ድንገተኛ ህልፈተ ህይወት ተከትሎ በርካቶች ሀሰባቸውን እየገለፁ ነው፡፡

በግብፅ ታሪክ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ስልጣን የያዙ የመጀመሪያው ሰው መሆናቸውን ገድላቸው ያሳያል- የ67 ዓመቱ የግብፅ የቀድሞ ፕሬዝዳንት መሐመድ ሙርሲ፡፡

ከስምንት ዓመታት በፊት በተለያዩ የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት የተቀጣጠለውን የአረብ አብዮትን ተከትሎ ግብፅን ለ30 ዓመታት የመሯት ሁስኒ ሙባረክ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ነበር መሐመድ ሙርሲ የግብፅ ፕሬዝዳንት መሆን የቻሉት፡፡

የዛሬ ሰባት ዓመት ሃገራቸው ግብፅ ባካሄደችው ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ላይ የህዝባቸውን ይሁንታ አግኝተው መንበረ ስልጣኑን የተረከቡት የሙስሊም ወንድማማቾች እና የግብፅ የቀድሞ መሪ ሙሐመድ ሙርሲ በተለይ በምጣኔ ሃብት ዘርፍ ለግብፃውያኑ አዲስ ለውጥ ባለማምጣታቸው ሰፊ ህዝባዊ ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር፡፡

ተቃውሞዉም በያኔው የመከላከያ ሚኒስትር አብዱል ፈታህ አልሲሲ በተመራ ጦር ድጋፍ መፈንቅለ መንግስት ተደርጎባቸው ከአንድ አመት ያልዘለለ የፕሬዝዳንትነት ጊዜ በኋላ ውሎ አዳራቸው ወህኒ ቤት ሆኖ ቆይታል፡፡

ወህኒ ቤት ሆነው በበርካታ ክሶች የፍርድ ሂደታቸውን ሲከታተሉ የቆዩት ሙርሲ ስኳርን እና ኩላሊትን ጨምሮ በተለያዩ የህመም አይነቶች ተጠቅተው እንደነበርም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው፡፡

ስድስት ዓመታትን ካይሮ በሚገኝ ማረሚያ ቤት ያለ ጠያቂ ጊዜአቸውን በእስር ያሳለፉት የማቴሪያል ኢንጅነሪንግ ዶክተሩ ሙርሲ ትናንት ከተከሰሱባቸው ጉዳዮች በአንዱ ላይ የፍርድ ሂደታቸውን እየተከታተሉ በቆዩበት ቅፅበት ራሳቸውን ስተው የወደቁ ሲሆን ከቆይታ በኋላ ህይወታቸው ማለፉን የግብፅ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ መርዶዉን አውጇል፡፡

የመሐመድ ሙርሲ ድንገተኛ ህልፈት በርካቶችን ያስቆጣው ሲሆን ስርዓተ ቀብራቸውም ዛሬ  መፈፀሙን ጠበቃቸው ይፋ አድርጓል፡፡

በርካታ ታዋቂ ግለሰቦችም ድንገተኛ ህልፈቱን አስመልክተው መልእክታቸውን እየገለፁ ነው፡፡

የኳታሩ ኢሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አልታኒ ‹‹የዶክተር መሐመድ ሙርሲ ድንገተኛ ህልፈት ስንሰማ ከባድ ሃዘን ነው የተሰማን፡፡

ለቤተሰቦቹ እና ለመላ ግብፃውያን የተሰማኝን ጥልቅ ሃዘን እገልፃለሁ፡፡ ሁላችንም የፈጣሪ ነን፤ ወደ እርሱም እንሄዳለን፡፡›› ሲሉ ሃዘናቸውን ገልፀዋል፡፡

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶጋን በበኩላቸው ‹‹ሙርሲን ወደ እስር በመወርወር ወደ ሞት የመሩት አንባገነኖችን መቼም ቢሆን ታሪክ አይረሳቸውም፤ አላህ የሰማእቱ ወንድማችንን ነፍስ በገነት ያኑራት›› ብለዋል፡፡

በሂዩማን ራይት ዋች የሰሜን አፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ ዋና ዳይሬክተር  ሳራህ ሊህ ዊትሰን ሁነቱ አሳዛኝ ግን ደግሞ የሚጠበቅ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አያይዘውም ‹‹ለበርካታ ዓመታት ስንሰንደው የነበረው መረጃ የሚያሳየው ሙርሲ በአሰቃቂ ሁኔታ ላይ እንደነበሩ እና ለፍርድ በሚቀርቡበት ወቅትም የግል የህክምና ክትትል እንዲደረግላቸው ይጠይቁ እንደነበር ነው ብለዋል፡፡

በቂ የምግብ አቅርቦት እና የህክምና አገልግሎት አያገኙም ነበር ይህን ደግሞ የግብፅ መንግስት በሚገባ ያውቃል፡፡

ክብደታቸውም በከፍተኛ ፍጥነት በመቀነሱ ፍርድቤት ላይ ራሳቸውን ስተዋል፡፡›› ሲሉ ለአልጀዚራ ገልፀዋል፡፡

ለዚህም የሃገሪቱ መንግስት ተጠያቂ ነው ብለዋል፡፡

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ የሙርሲ የአሟሟት ሁኔታን ጨምሮ ለብቻቸው የታሰሩበት ምክንያት ገለልተኛ ጥናት እንዲደረግ ሲል ጠይቋል፡፡/አልጀዚራ/