ተመድ በሊቢያ የተፈጸመው የጦር ወንጀል ሊሆን ይችላል አለ

የተባበሩት መንግሥታት በሊቢያ የተፈጸመው ጥቃት የጦር ወንጀል ሊሆን እንደሚችል ገለጸ፡፡

በሊቢያ የስደተኞች ማቆያ ላይ በደረሰ የአየር ጥቃት በትንሹ 44 ስደተኞች መሞታቸውን እና ቢያስ 130 ሰዎች ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የሊቢያ መንግሥት አስታውቋል።

ከሞቱት መካከል አብዛኞቹ አፍሪካውያን ስደተኞች ናቸው ተብሏል።

በተባበሩት መንግሥታት እውቅና የተሰጠው የሊቢያ መንግሥት ለጥቃቱ በጄነራል ካሊፍ ሃፍታር የሚመራውን ቡደን ተጠያቂ አድርጓል።

የተባበሩት መንግሥታት ኃላፊዎች ከመዲናዋ ወጣ ባለ የስደተኞች ማቆያ ላይ የደረሰውን ጥቃት የጦር ወንጀል ሊያስብለው የሚችል መስፈርቶች አሟልቷል ብለዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሊቢያ ወደ አውሮፓ መሻገር ለሚፈልጉ ስደተኞች መነሻ ሆናለች።

ሊቢያን ለረዥም ጊዜ ሲያስተዳድሯት የነበሩት ሙአመድ ጋዳፊ እ.ኤ.አ በ2011 ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ አገሪቱ በግጭት እየታመሰች ሲሆን፤ የተለያዩ የጦር አበጋዞች በሚቆጣጠሯቸው ስፍራዎች ተከፋፍላም ትገኛለች። በርካታ ስደተኞች በመንግሥት እስር ቤቶች ውስጥ ታጉረው ይገኛሉ።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ሚሼል ባቼሌት ማክሰኞ ዕለት ጥቃት የተሰነዘረበት እስር ቤት በሊቢያ ለሚንቀሳቀሱ የጦር ቡድኖች በሙሉ በስፍራው ሲቪል ሰዎች ብቻ እንደሚኖሩበት መረጃ ተላልፏል ብለዋል።

"ይህ ጥቃት የተፈጸመበተን ሁኔታ ስንመለከት በትክክልም ከጦር ወንጀለኝነት ጋር የሚስተካከል ነው" ብለዋል። በመጠለያው ላይ ጥቃት ሲሰነዘር ይህ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ኮሚሽነሯ ጨምረው ተናግረዋል።

የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በጥቃቱ እጅግ ማዘናቸውን እና ጥፋተኞችን ወደ ፍርድ ለማቅረብ ገለልተኛ አጣሪ ቡድን ጉዳዩን እንዲመረምር አዘዋል።

የኤኤፍፒ ዘገባ እንደጠቆመው የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ካውንስል የተፈጸመውን ጥቃት በማውገዝ መግለጫ ለማውጣት ቢሰበሰብም ተሳታፊዎች ሳይስማሙ ስበሰባው ተጠናቋል። እንደዘገባው ከሆነ የአሜሪካ ተወካዮች በመግለጫው ላይ ፊርማቸውን ከማኖራቸው በፊት ከዋሽንግተን ፍቃድ ማግኘት ይኖርብናል ማለታቸው መግለጫው እንዳይወጣ አድርጓል።

ታጅኡራ የሚባለው እስር ቤት 600 ስደተኞችን በውስጡ የያዘ ሲሆን፣ ማክሰኞ ዕለት የተፈጸመው ጥቃት ያነጣጠረውም በእስር ቤቱ ላይ ነበር።

ከተጎጂዎቹ መካከል ሴቶች እና ህጻናት እንደሚገኙበት የተባበሩት መንግሥታት ባልደረባ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የሊቢያ መንግሥት የጤና ሚኒስትር የሆኑት ዶ/ር ካሃሊድ ቢን አቲያ ጥቃቱ የተሰነዘረበትን ስፍራ ለቢቢሲ ሲገልጹ "ሰው በየስፍራው ነበር፣ መጠላያ ካምፑ ወድሟል፣ ሰዎች እያለቀሱ ነው፣ አከባቢው በደም ተሸፍኗል፣ መብራት ተቋርጧል" ብለዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ በሊቢያ ተሻግረው አውሮፓ ለመድረስ የሚያስቡ ስደተኞች የሚቆዩት መንግሥት በሚቆጣጠራቸው የስደተኛ ማቆያዎች ሲሆን፣ አብዛኞቹ መጠለያዎች የሚገኙት ከአማፂያን ጋር ጦርነት በሚደረግባቸው ስፍራዎች ነው።

በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የእነዚህ መጠለያ ጣቢያዎች አያያዝ ትችት ይቀርብበታልም ነው የተባለው። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)