ተመድ በሊቢያ የሚገኙ የስደተኛ ማጎሪያዎች በሙሉ እንዲዘጉ ጠየቀ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሊቢያ የሚገኙ የስደተኛ ማጎሪያዎች በሙሉ እንዲዘጉ ጠየቀ።

ድርጅቱ ይህን ያለው እስር ቤቶቹ ስደተኞችን ለመያዝ የሚያስችል መስፈርትን አያሟሉም በማለት ነው።

ከሁለት ሳምንታት በፊት በሊቢያ የስደተኞች ማቆያ ላይ በደረሰ የአየር ጥቃት በትንሹ 50 ስደተኞች መሞታቸውን እና ቢያንስ 130 ሰዎች ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የሊቢያ መንግሥት ማስታወቁ ይታወሳል።

የሊቢያ መንግሥት ለጥቃቱ በጄነራል ካሊፍ ሃፍታር የሚመራውን ቡደን ተጠያቂ ያደረገ ሲሆን፣ ከሟቾቹ መካከል አብዛኞቹ አፍሪካውያን ስደተኞች መሆናቸው ታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት ይህን በስደተኞች መጎሪያ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት የጦር ወንጀል ሊሆን ይችላል ሲል ገልጾት ነበር።

በሊቢያ መንግሥት የሚተዳደሩ እስር ቤቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን በተጎሳቆለ መንገድ በውስጣቸው ይዘዋል።

በቅርቡ የተፈጸመውን የአየር ጥቃት በማስታወስ እስር ቤቶቹ ለስደተኞች ህይወት አስጊ መሆናቸውን በመጥቀስ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ ማጎሪያ ማዕከሎቹ በፍጥነት እንዲፈርሱ እና ስደተኞቹም በአካባቢው ወደሚገኙ ማህበረሰብ አባላት እንዲቀላቀሉ ጠይቋል።

ተመድ ጨምሮም ስደተኞቹን ከሕብረተሰቡ ጋር ከተቀላቀሉ በኋላ ሊረዳቸው ዝግጁ እንደሆነ ጠቅሷል።

ከሁለት ሳምንታት በፊት የአየር ጥቃት የተሰነዘረበት የስደተኞች ማጎሪያ ታጅኡራ፤ በውስጡ 600 ስደተኞችን ይዟል። የተፈጸመው የአየር ጥቃትም ያነጣጠረው በእስር ቤቱ ላይ ነበር።

ከተጎጂዎቹ መካከል ሴቶች እና ህጻናት እንደሚገኙበት የተባበሩት መንግሥታት ባልደረባ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሊቢያን ተሻግረው አውሮፓ ለመድረስ የሚያስቡ ስደተኞች የሚቆዩት መንግሥት በሚቆጣጠራቸው የስደተኛ ማቆያዎች ሲሆን፣ አብዛኞቹ መጠለያዎች የሚገኙት ከአማፂያን ጋር ጦርነት በሚደረግባቸው ስፍራዎች ነው።

ለጥቃቱ ተጠያቂ የተደረገው የጄነራል ካሊፍ ሃፍታር ቡደን ከእስር ቤቱ አቅራቢያ የሚገኝ የመንግሥት ካምፕ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ከዚያም የመንግሥት ደጋፊ የሆኑ ኃይሎች አጸፋዊ እርምጃ መውሰዳቸውንና ቡድኑ በድጋሚ በወሰደው እርምጃ በስህተት እስር ቤቱ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን አምኗል። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)