በሜዲትራኒያን ባህር ላይ በገጠመ የመስጠም አደጋ 145 ስደተኞች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተገለፀ

ስደተኞችን ይዘው ወደ ጣሊያን በማምራት ላይ የነበሩ ጀልባዎች ሜዲትራኒያን ባህር ላይ ሰጥመው 145 ያህል ስደተኞች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተገለፀ፡፡

ጀልባዎቹ ከሊቢያ 300 ስደተኞችን ጭነው ወደ ጣሊያን ሲያመሩ ነበር በሊቢያ የባህር ዳርቻ የሰጠሙት።

ጀልባዎቹ ከትሪፖሊ ምስራቃዊ የባህር ዳርቻ 120 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መስጠማቸውን የሊቢያ የባህር ላይ ጠባቂዎች ቃል አቀባይ አዩብ ቃሲም ገልፀዋል፡፡

ከተሳፋሪዎቹ መካከል 134 ያህሉን ማትረፍ መቻሉን የገለጹት ቃል አቀባዩ÷ ከአደጋው ሰለባዎች መካከል ሴቶችና ህፃናት እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡

ከስደተኞች መካከል የኢትዮጵያ፣ ፍልስጤም፣ ኤርትራና ሱዳን ዜጎች እንደሚገኙበት ጠቁመዋል፡፡

ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት በበኩሉ ከ150 በላይ ስደተኞች በአደጋው ሳቢያ ሳይሰጥሙ እንደማይቀር በትዊተር ገጹ  አስፍሯል።

የአውሮፓ ህብረት በሊቢያ ስደተኞችን የማቆየት ተግባር እንዲቆም ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ በቀጠናው የነፍስ አድን ተልዕኮውን ማቋረጡ ይታወሳል።

(ምንጭ፡- አልጀዚራ)