ደቡብ አፍሪካዊያን ታዳጊ አብራሪዎችን ሲረዱ የነበሩት ፓይለቶች በአውሮፕላን አደጋ ሞቱ

ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ ሃገራት አየር ላይ ከበረሩት ደቡብ አፍሪካዊያን ታዳጊ አብራሪዎች ጀርባ ሆነው ፕሮጀክቱን ሲያስተባብሩ የነበሩ ሁለቱ ደቡብ አፍሪካዊያን ፓይለቶች ቅዳሜ ዕለት ታንዛንያ ውስጥ ባጋጠማቸው የመከስከስ አደጋ ህይወታቸው አለፈ።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ደቡብ አፍሪካዊያኑ ታዳጊዎች በገጣጠሟት አውሮፕላን ከደቡብ አፍሪካ ተነስተው ካይሮ መዲና ግብፅ መግባታቸው የሚታወስ ነው፤ ከታዳጊዎቹ ጀርባ ደግሞ ሁለት ፓይለቶች ፕሮጀክቱ እንዲሳካ ጥረት አድርገዋል።
ዴስ ዌርነርና ዌርነት ፍሮንማን የተባሉት ፓይለቶች ታዳጊዎቹ የሚያበሯትን አውሮፕላን ከኋላ አጅበው በመቆጣጠር በጉዟቸው ይከተሏቸው ነበር።
ደቡብ አፍሪካ በዛሬው ዕለት እንደሚደርሱ ይጠበቅ የነበረ ቢሆንም፣ ከታንዛንያ ታቦራ አየር ማረፊያ የተነሱት አብራሪዎቹ ቅዳሜ ዕለት መከስከሳቸውን የታንዛንያ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ፓይለቶቹ ከእይታ ከመጥፋታቸው በፊት የሞተር ችግር እንዳጋጠማቸው መልዕክት ማስተላለፋቸውን የታንዛንያ የአየር ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታውቋል።
አውሮፕላኗ ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ የሆነች ሲሆን፣ ማግኘት የተቻለውም ጥቂት አካሏን መሆኑንም ባለስልጣናቱ አክለው ተናግራዋል።
አውሮፕላኗ ባለቤትነቷ ዩ ድሪም ግሎባል የሚባል ድርጅት ሲሆን፣ ይህም ከታዳጊዎቹ ፓይለቶች አንዷ ሜጋን ዌርነርና አሁን ህይወቱ ያለፈው አባቷ ዴስ ዌርነር ነው።
"ከኬፕታውን ካይሮ ታዳጊዎቹን አጅባ ስትበር የነበረችው አውሮፕላን መከስከሷን መስማት ያሳዝናል፤ የፕሮጀክቱ ጠንሳሾች ዴስ ዌርነርና ዌርነር ፍሮምናንም ህይወታቸውን አጥተዋል። ሌላ አደጋ የደረሰበት ሰው የለም" ሲል ድሪም ግሎባል በፌስቡክ ገፁ ይህንን መልዕክት አስፍሯል።
ሁለቱ ፓይለቶች የታዳጊዎቹን አብራሪዎች አውሮፕላን ፕሮጀክት ከጅምሩ የጠነሰሱት ሲሆን፣ በዳይሬክተርነትም እየመሩት ነበር ተብሏል።
ታዳጊዎቹ የሚያበሯት አራት መቀመጫ ያላት አውሮፕላን ከተለያየ ስፍራ በተውጣጡ 20 ተማሪዎች ነው የተገጣጠመችው።
ይህንን ፕሮጀክት የጀመረችው የ17 ዓመቷ ሜጋን ሲትሆን፣ አንድ ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎች ፍላጎታቸውን ቢያሳዩም ባደረጉት ማጣራት 20 ተማሪዎች ተመርጠዋል።
ስድስቱም ታዳጊዎች የአብራሪነት ፍቃድ ያገኙ ሲሆን፣ 12 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት በረራም በስድስቱ ትከሻ ላይ ወድቆ ነበር።
በሦስት ሳምንት ጉዟቸውም ናሚቢያ፣ ኢትዮጵያ፣ ማላዊ፣ ዛንዚባር፣ ዩጋንዳ የመሳሰሉ አገራትን አካልለዋል።
ታዳጊዎቹ አውሮፕላኗን ሰርቶ ለማጠናቀቅ ሦስት ሳምንታት የፈጀባቸው ሲሆን፤ የውስጥ አካሏን ከደቡብ አፍሪካ አውሮፕላን አምራች ኩባንያ በመግዛት እንዲሁም በሺህዎች የሚቆጠሩ የውስጥ አካሏን መገጣጠም ችለዋል።
አንዳንድ የአውሮፕላኑ ክፍሎችና ሞተሩ በሰለጠኑ ሰዎች የተገጠሙ ሲሆን፣ አጠቃላይ አውሮፕላኑ የተገጣጠመው በታዳጊዎቹ ነው። (ምጭ፡-ቢቢሲ)