በዴሞክራቲክ ኮንጎው ጀልባ ሰጥሞ 34 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ

በዴሞክራቲክ ኮንጎ፤ በኮንጎ ወንዝ ላይ መንገደኞችን ጭኖ ሲጓዝ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ ጀልባ ሰጥሞ ቢያንስ የ34 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ ተገለጸ።

ፖሊስ እንዳስታወቀው ከአደጋው 76 ተሳፋሪዎች በህይወት መትረፍ የቻሉ ሲሆን፣ በወቅቱ ጀልባው ከአቅሙ በላይ በጣም ብዙ ሰው ሳይጭን እንዳልቀረ ተገምቷል።

ጀልባው ከሀገሪቱ ዋና ከተማ ኪንሻሳ በመነሳት ማይ ንዶምቤ ወደተባለችው ሰሜናዊ ግዛት እየተጓዘ ነበር።

የአደጋው መንስኤ እስካሁን እንዳልታወቀ የገለጸው ፖሊስ ተሳፋሪዎቹ የውሃ ላይ መንሳፈፊያ ጃኬቶችን አድርገው ነበር ብሎ ለማሰብ እጅግ አስቸጋሪ ነው ብሏል።

በዴሞክራቲክ ኮንጎ የውሃ ላይ ጉዞ በጣም የሚዘወተር ሲሆን፣ ጀልባዎች የተለያዩ ጭነቶችና ተሳፋሪዎች ከአቅም በላይ ጨነው ሲጓዙ መመልከት የተለመደ ነው።

እስከ 40 ሜትር የሚደርስ ከፍታ ያላቸውና አንዳንዴም ባለሁለት ክፍል ትልልቅ ጀልባዎች ግልጋሎት ላይ ሲውሉ ይስተዋላል። ሁሉም ተሳፋሪዎች ደግሞ ውሃ ዋና ይችላሉ ብሎ ማሰብ ከባድ ነው።

የዴሞክራቲክ ኮንጎ የአስፋልት መንገዶች በጣም የተበላሹና ከጥቅም ውጪ በመሆናቸው ብዙ የሀገሬው ሰዎች በጀልባ የሚደረጉ ጉዞዎችን ምርጫቸው ያደርጋሉ። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)