ደቡብ አፍሪካ ናይጄሪያን ይቅርታ ጠየቀች

ደቡብ አፍሪካ በውጭ አገራት ዜጎች ላይ ከደረሰው ጥቃት ጋር በተያያዘ ናይጄሪያን ይቅርታ መጠየቋ ተነግሯል፡፡

በደቡብ አፍሪካ ናይጄሪያውያንን ጨምሮ በውጭ አገራት ዜጎች ላይ በተሰነዘረ ጥቃት ህይወት ጠፍቷል፤ በርካታ ንብረትም ተዘርፏል፡፡

በዚህ ሳቢያ ሁለቱ አገራት ግንኙነታቸው ሻክሮ ከቆየ በኋላ አሁን ደቡብ አፍሪካ ናይጄሪያን ይቅርታ ጠይቃለች፡፡

የደቡብ አፍሪካ ልዮ መልዕክተኛ ጄፍ ራዴቤ የፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳን የይቅርታ ደብዳቤ ለናይጄሪያው መሪ ሙሐመዱ ቡሐሪ አድርሰዋል፡፡

ደቡብ አፍሪካ ናይጄሪያውያንን ጨምሮ በውጭ አገራት ዜጎች ላይ ጥቃቱን በሰነዘሩ ሰዎች ላይ እርምጃ መውሰዷን ልዮ መልዕክተኛው ተናግረዋል፡፡

በአገሪቱ በተከሰተው ግጭት የ10 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በርካቶች ተፈናቅለዋል፤ ንብረታቸውም ተዘርፏል ነው የተባለው፡፡

ሁለቱ አገራት በተፈጠረው ችግር የሻገረ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል እየሰሩ ቢሆንም ናይጄሪያ ዜጎቿን ከደቡብ አፍሪካ እያስወጣች ትገኛለች፡፡

(ምንጭ፦ ቢቢሲ)